የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) እና ሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ፤ እድሎች እና ተግዳሮቶች በሚል ርእስ ለኮሚሽኑ ሠራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል። መድረኩ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በኢትዮጵያ መስፋፋት በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚኖረውን አንድምታ አስመልክቶ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው።

በመድረኩ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ምንነት፣ የቴክኖሎጂው ፈጣን እድገት በሰብአዊ መብቶች ላይ ያለው አዎንታዊ እና አሉታዊ አስተዋጽዖ፣ እንዲሁም ለሰብአዊ መብቶች መከበር እና መጠበቅ ስለሚያደርገው አበርክቶ ገለጻ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሁለንተናዊ የሰው ልጅ መብቶች ጥበቃን ለማሻሻልና ለማጠናከር ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑ ተብራርቷል። በተለይም ቴክኖሎጂው እንደ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ ፍልሰተኞች፣ ስደተኞች እና ሌሎች ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች እገዛ ጥቅም ላይ የሚውሉ መፍትሄዎችን ከማቅረብ እና የመረጃ እና የአገልግሎት ተደራሽነትን ከማሳደግ አኳያ ያለው አዎንታዊ አበርክቶ ከተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች አንጻር ሰፊ ዳሰሳ ቀርቦበታል።

በሌላ በኩል ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰብአዊ መብቶች መርሖችን ባገናዘበ ሁኔታ አገልግሎት ላይ ካልዋለ አድሏዊነትን የማስፋፋት፣ ፍትሕ የማዛባት እንዲሁም የግል መረጃ ጥበቃ እና ሐሳብን በነጻነት መግለጽን ጨምሮ በአጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች መከበር እና መጠበቅ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የማስከተል ዐቅም ያለው መሆኑ በአሳሳቢነት ተነስቷል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ሚዛኔ አባተ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በሰብአዊ መብቶች ላይ ያለውን አዎንታዊና አሉታዊ አስተዋጽዖ በአግባቡ ተረድቶ አጠቃቀሙ ሰብአዊ መብቶችን ያከበረ እንዲሆን ለማድረግ የኢሰመኮ የባለሙያዎችን ዐቅም ማሳደግ፤ እንዲሁም ተቋማዊ አሠራርንም ከዚህ አዲስ ሁኔታ ጋር ማጣጣም እንደሚገባ ገልጸዋል። አክለውም ኢሰመኮ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዙሪያ የሚያከናውናቸው ተግባራት የተካተቱበት የአምስት ዓመት 2019- 2023 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ ከ2026-2030) ስትራቴጂክ ዕቅድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡