የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ እና ከፍተኛ አመራሮች ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የጥቃት ተጎጂዎች መብቶች ተሟጋች ናጅላ ናሲፍ ፓልማ ጋር መጋቢት 2 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ በባ፣ በኢሰመኮ ዋና መሥሪያ ቤት ተወያይተዋል። ውይይቱ የተካሄደው ተሟጋቿ የተጎጂዎችን መብቶች ጥበቃ እና ከጉዳት ላገገሙ የጥቃት ሰለባዎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍን ለማጠናከር የተሰጣቸውን ኃላፊነት መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ እያደረጉት ባለው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወቅት ነው። የውይይቱ ዓላማ ትብብርን ማጠናከር እና ተጎጂን ማእከል ያደረጉ ሥልቶች ትግበራን ማጎልበት፤ የተጎጂዎችን መብቶች፣ ድምጽ እና ፍላጎቶች መሠረት ያደረጉ ተቋማዊ ምላሾችን እና የድጋፍ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ ነው።

በውይይቱ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ ለተጎጂዎች መብቶች ተሟጋቿ ስለ ኢሰመኮ ሥልጣን፣ ተግባር እና ለተጎጂዎች ስላለው አጋርነት ማብራሪያ ሰጥተዋል። ኢሰመኮ ተጎጂዎች እንዲካሱ የሚያደርገውን ውትወታ፣ የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ተጎጂዎችን ማእከል ያደረገ መሆኑን ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለውን የክትትል ሥራ፣ እንዲሁም የሴቶችና የሕፃናት መብቶችን ለማስከበር ባደራጀው ልዩ የሥራ ከፍል የሚያከናውናቸው ተግባራትን አብራርተዋል። በተጨማሪም አመራሮቹ ኢሰመኮ በክትትልና ምርመራ፣ ምክረ ሐሳቦችን በመስጠት፣ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን በማመቻቸት፣ የሥነ-ልቦና ድጋፍ መኖሩን በማረጋገጥ፣ የቅብብሎሽ ሥርዓቶችን (referral mechanisms) በማጠናከር እና ተጎጂዎች ካሳ እንዲከፈላቸው በመሟገት ረገድ እያከናወናቸው ያሉትን ዝርዝር ተግባራት አቅርበዋል።

የጥቃት ተጎጂዎች መብቶች ተሟጋቿ በበኩላቸው የኢሰመኮን ጥረት አድንቀው፤ በዓለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የጾታዊ ብዝበዛ እና ጥቃት ፈጻሚዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በሚደረጉ ጥረቶች ያሉ ተግዳሮቶችን አንስተዋል። ግልጽ የሆኑ የተጠያቂነት እርምጃዎች መወሰድ እንዲሁም ወቅታዊና ውጤታማ ምላሽ እንዳይሰጥ እንቅፋት የሚሆኑ ክፍተቶችን ለመድፈን ጠንካራ የሪፖርት አቀራረብና የክትትል ሥርዓቶች መኖር እንዳለባቸውም ተሟጋቿ አጽንዖት ሰጥተዋል። ተሟጋቿ አክለውም እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት የተጎጂዎችን የሕይወት ተሞክሮ ማእከል ያደረጉ ፖሊሲዎች እና ተግባራት እንዲቀረጹ እንዲሁም ፍትሕና ድጋፍ ለሁሉም ተጎጂዎች ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ውይይቱ ተጎጂዎችን በመደገፍ፣ ተአማኒነትን በመገንባት እና ለተጎጂዎች መብት መከበር ቅድሚያ በመስጠት ረገድ የኢሰመኮን ተሞክሮዎች መማር ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በውይይቱ የተጎጂዎች ድጋፍ፣ ክትትል እና ተሟጋችነት ሥራዎችን ለማጠናከር የሚያስችሉ የትብብር ዕድሎችም ተመላክተዋል።

ውይይቱ የተጎጂዎች መብቶች ተሟጋቿ ወጥ የሆነ፣ ሁሉን አቀፍ እና ተጎጂዎችንና ከጉዳት ያገገሙ የጥቃት ሰለባዎችን (victims and survivors) ማእከል ያደረገ ጥቃትን የመከላከል፣ ምላሽ የመስጠት እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት፣ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ከቀጠናዊ አካላት ጋር በመወያየት የሚያደርጓቸው ሰፊ ጥረቶች አንድ አካል ነው።