የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምሥራቅ ጉራጌ ዞን እንሴኖ ከተማ እና በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ እንዲሁም አካባቢው በሚገኙ ወረዳዎች ከየካቲት 6 እስከ 27 ቀን 2018 ዓ.ም. በተንቀሳቃሽ አቤቱታ መቀበያ ማእከል የተቀበላቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ጉዳዮችን አስመልክቶ ከክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መጋቢት 4 ቀን 2018 ዓ.ም የውይይት መድረክ በሆሳዕና ከተማ አካሂዷል።

በውይይቱ ኢሰመኮ በተንቀሳቃሽ የአቤቱታ ቅበላ መርኃ ግብሩ ከተቀበላቸው አጠቃላይ 323 አቤቱታዎች መካከል አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች መፍትሔ እንዲያገኙ ተደርጓል። ከነዚህም መካከል በአማካይ ከ11 አስከ 25 ቀናት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር የቆዩ ተጠርጣሪዎች እንዲፈቱ፤ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ እንዲሁም ከቤተሰብ ጥየቃና ህክምና አገልግሎት ጋር በተያያዘ የቀረቡ አቤቱታዎች እልባት እንዲያገኙ መደረጉ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ኢሰመኮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት በመሥራት እና የውትወታ ተግባራትን በማከናወን ያስመዘገባቸው አበረታች ውጤቶች እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።


የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሕግ ጉዳዮች አማካሪ ኑርዬ ሱሌ፤ ኢሰመኮ በ2017 ዓ.ም. በክልሉ ባከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክትትሎች መነሻነት የሰጣቸውን ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ በማድረግ የተገኙ አዎንታዊ ውጤቶችን ጠቅሰው፤ በዚህ ተንቀሳቃሽ የአቤቱታ ቅበላ መርኃ ግብር መነሻነት የተሰጡ ተጨማሪ ምክረ ሐሳቦች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ለሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች መመሪያ ሰጥተዋል።

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ሪጅናል ዳይሬክተር በጋሻው እሸቱ ኢሰመኮ በተንቀሳቃሽ አቤቱታ ቅበላ መርኃ ግብር ለማኅበረሰቡ ቅርብ በመሆን የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ ክልሉ ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታውን የማሻሻል ጥረቶችን ይበልጥ እንዲያጠናክር እና ባለድርሻ አካላትም የሰብአዊ መብቶች ጥበቃና መከበርን ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።