የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ እና የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ፕሬዝደንት ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የቀድሞውን የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ክቡር አምባሳደር ጥሩነህ ዜናን ሚያዚያ 3 ቀን 2018 ዓ.ም. በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተው ጎብኝተዋል። ክቡር አምባሳደር ጥሩነህ ኢሰመኮን ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. በዋና ኮሚሽነርነት የመሩ ናቸው።

ክቡር ከአምባሳደር ጥሩነህ ከሕይወት ተሞክሯቸው እና ከሥራ ልምዳቸው በመነሳት በሰጡት ምክር፦ “ሰው የሚያከብር ሰው ራሱን ያከብራል፣ እራሱን የሚያከብር ሰው ደግሞ ሥራውን በአግባቡ ይሠራል፤ ሀገርንም ያከብራል። አክብራችሁ ልትጠይቁኝ ስለመጣቸሁ አመሰግናለሁ!” ብልዋል። ኢሰመኮ አሁን እያከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ እንዲሁም ከቀጠናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት አጠንክሮ እንዲቀጥልም መክረዋል።

በተጨማሪም የኢሰመኮ ኮሚሽነሮች፣ የሥራ መሪዎች እና ባለሙያዎች በውጭ ሀገራት በሥራ አጋጣሚ የሚያገኟቸውን ዕውቀቶች እና መልካም ተሞክሮዎች በሀገር ውስጥ እንዲተገበሩ እንዲሁም ኮሚሽኑ ተቋማዊ ዐቅሙን ማስቀጠል እንዲችል ባለሙያዎችን ማቆየት እና መተካካትን የሚያረጋግጥ አሠራር እንዲያመቻች አሳስበዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በበኩላቸው የአምባሳደሩን መልካም ምኞች መሠረት በማድረግ ኢሰመኮ ነጻነቱን ጠብቆ የሰብአዊ መብቶች ተግባራቱን የሚያከናውን፣ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ድምጹ የሚሰማ ጠንካራ ተቋም ሆኖ እንደሚቀጥል አረጋግጠውላቸዋል። ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አክለውም ፈጣሪ ለአምባሳደር ጥሩነህ ረጅም ዕድሜና ጤና እንዲሰጣቸው ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።