የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የማኅበረ ሥነ-ልቦና ጉዳት (psychosocial disability) ያለባቸው ሰዎች የጤና መብት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረገው የሰብአዊ መብቶች ክትትል በተለዩ ግኝቶች እና በቀረቡ ምክረ ሐሳቦች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 12 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ አካሂዷል። ክትትሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች ሥር በሚገኙ 13 የመንግሥት ሆስፒታሎች እና የግል የሕክምና ማእከላት ላይ የተካሄደ ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም እንደ ከባድ ድብርት፣ ባይፖላር ዲስኦርደር፣ ስኪዞፌርንያ፣ የጭንቀት ሕመም ባሉ የረዥም ጊዜ የአእምሮ ጤና ጉዳቶች ምክንያት ለተግባር ውስንነቶች (functional limitations) እና ለማኅበራዊ እንቅፋቶች (social barriers) የተጋለጡ ሰዎችን የሕክምና አገልግሎት ሁኔታዎችን ለመለየት እንዲሁም የመፍትሔ ሐሳቦችን ለማመልከት ያለመ ነው።


በምክክር መድረኩ ላይ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ ከትምህርት እና ከጤና ሚኒስቴር፤ ክትትሉ ከተካሄደባቸው ክልሎች የጤና፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች፣ ከአካል ጉዳተኞች ማኅበራት እና የጤና ተቋማት የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ኢሰመኮ በክትትሉ በለያቸው ቁልፍ እመርታዎች፣ አሳሳቢ ጉዳዮች እና ምክረ ሐሳቦች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። ተሳታፊዎች በማኅበረ ሥነ-ልቦና ጤና አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን፣ በተቋሞቻቸው እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን እና የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች አቅርበዋል።


በክትትሉ ከተለዩ አዎንታዊ ሁኔታዎች መካከል የአእምሮ ሕክምና ቀደም ካሉት ዓመታት በተለየ በአንድ ሆስፒታል ሳይወሰን በተለያዩ ሪፈራል እና የማስተማሪያ ሆስፒታሎች ውስጥ እየተሰጠ መሆኑ፣ ታካሚዎች የአእምሮ ሕክምናን በቅርበት እንዲያገኙ መደረጉ፣ ክትትል በተደረገባቸው ተቋማት የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ታካሚዎችን በመልካም ሥነ ምግባር እና አያያዝ የሚያስተናግዱ መሆኑ እንዲሁም በመንግሥት የሕክምና ተቋማት ከሱስ ሕክምና ውጪ ያሉ የአእምሮ ሕክምናዎች እና መድኃኒቶች በጤና መድኅን ሽፋን ለተጠቃሚው እንዲሰጡ መደረጉ ተጠቃሽ ናቸው።


በሌላ በኩል ክትትሉ በተከናወነባቸው የመንግሥት የጤና ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የመድኃኒት እጥረት መኖሩ፣ እንደ የኤሌክትሪክ ንዝረት ሕክምና (Electroconvulsive therapy) ያሉ አስፈላጊ የሕክምና ዘዴዎችና ቴክኖሎጂዎች በበቂ ያልተሟላ መሆኑ፣ በሀገሪቱ ለአእምሮ ሕክምና ተጠቃሚ ሕፃናት ተብሎ የተዘጋጀ የመድኃኒት መጠን (ዶዝ) እና የመድኃኒቶች እጥረት መኖሩ፣ በግጭት ዐውድ ውስጥ በሚገኙ ክልሎች የማኅበረ ሥነ-ልቦና ሕክምና ፈላጊ ታካሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ቁጥር ውስን መሆኑ እና በጤና ተቋማት የሚስተዋለው ከፍተኛ የበጀት ውስንነት አሳሳቢ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቅሷል።
በምክክሩ ማጠቃለያ ላይ ተሳታፊዎች በኢሰመኮ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን ለመፈጸም የሚያስችል የድርጊት መርኃ ግብር አዘጋጅተዋል።

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር መሐመድ አሕመድ፣ ሰዎች ሕይወታቸውን በአግባቡ እንዲመሩ፣ እንዲማሩ፣ እንዲሠሩ እና ለማኅበረሰባቸው የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ የአእምሮ ጤና መሠረታዊ መነሻ መሆኑን ጠቁመው፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለአእምሮ ጤና ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት፣ ተገኝነትና ጥራት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ አሳስበዋል።