የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ4 ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በሚገኙ 13 የተሐድሶ ማእከላት እና የጤና ተቋማት ላይ የአካል ጉዳተኞች የተሐድሶ አገልግሎት እና አጋዥ መሣሪያዎች የማግኘት መብትን አስመልክቶ ባካሄደው የሰብአዊ መብቶች ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል። ክትትሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ትግራይ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ የተሐድሶ ማእከላት እና የሪፈራል ሆስፒታሎች ላይ የተከናወነ ነው፡፡

በውይይቱ ላይ የጤና፣ የትምህርት እና የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የሕክምና ተቋማት፣ የአካል ተሐድሶ ማእከላት፣ የክልል ጤና ቢሮዎች፣ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት እንዲሁም ሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩም የተሐድሶ አገልግሎት ምንነት እንዲሁም የተሐድሶ አገልግሎትን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎች ላይ ገለጻ ተደርጓል። በተጨማሪም በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል የተለዩ አዎንታዊና አሳሳቢ ሁኔታዎች ቀርበዋል። የተሐድሶ አገልግሎትን የተመለከቱ የሕግ ማዕቀፎች መኖራቸው፣ አንዳንድ አጋዥ መሣሪያዎችና ቁሳቁሶች በሀገር ውስጥ መመረት መጀመራቸው፣ የዘርፉ ባለሙያዎች ሙያዊ ሥነ ምግባርን የተከተለ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ፣ የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት በንጽጽር የተሻለ የአጋዥ መሣሪያዎች አቅርቦት ያለው መሆኑ በአዎንታዊ ሁኔታ ተጠቅሰዋል።

በአንጻሩ የተሐድሶና አጋዥ መሣሪያዎች አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አነስተኛ መሆን፤ ሩቅና ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ የገጠር አካባቢዎች ተደራሽ አለመሆን፤ በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት መኖር እና የተሐድሶ አገልግሎት ትምህርት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አለመሰጠት በአሳሳቢነት የተለዩ ነጥቦች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም የአጋዥ መሣሪያዎች፣ ቴክኖሎጂዎች እና ማሽኖች አቅርቦት እጥረት፤ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ መሣሪያዎችና ማሽኖች ያረጁና የተበላሹ መሆናቸው፤ የተሐድሶ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ምቹ አለመሆን፤ ለሁሉም የአካል ጉዳት ዓይነቶች አገልግሎት የሚሰጥ ሁሉን አቀፍ (comprhensive) የተሐድሶ አገልግሎት አለመኖር፤ ዘርፉ የሚመራበት የፖሊሲ ማዕቀፍና የድርጊት መርኅ ግብር አለመኖር እና ከፍተኛ የበጀት እጥረት መሻሻል የሚገባቸውና በአሳሳቢነት የተጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የተሐድሶ አገልግሎት የሚፈልገው የሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ የተሐድሶ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በመሣሪያና በሰው ኃይል እንዲደራጁ፣ ዘርፉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት፣ መንግሥት የተሐድሶ አገልግሎት ፖሊሲ በመቅረጽ ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጥ እና በቂ በጀት እንዲመድብ እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በስፋት እንዲያከናውን ጠይቀዋል።

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር መሐመድ አሕመድ የአካል ጉዳተኞች የተሐድሶ እና አጋዥ መሣሪያዎች አገልግሎት የማግኘት መብት እንዲረጋገጥ ኢሰመኮ የሚያከናውናቸውን የክትትል እና የውትወታ ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ አክለውም፣ በክትትል ግኝቶቹ መነሻነት የቀረቡ ምክረ ሐሳቦች እንዲፈጸሙ፣ በዘርፉ እያጋጠመ ያለው የአጋዥ መሣሪያዎችና የሰው ኃይል አቅርቦት እጥረት እንዲቀረፍ፣ የተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ እንዲሻሻል እንዲሁም ተቋማት ተደራሽ እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ እና በትብብር እንዲሠሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።