የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር እና ኃላፊነት ለመወጣትና ለቀጣይ 5 ዓመታት የሚመራበት የ2019-2023 ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ የባለድርሻ አካላት ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ግንቦት 17 እና 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ የሁሉም ክልላዊ መንግሥታት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኩ ላይ ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ባለፉት 5 ዓመታት ሲተገበር የቆየው ስትራቴጂክ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የአዲሱ ስትራቴጂክ ዕቅድ ረቂቅ ይዘቶች ላይ በስፋት ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ከመከሰታቸው በፊት መከላከልን መሠረት ያደረገ (Preventive-focused) ተቋማዊ አሠራር መገንባት፤ ኢሰመኮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ እንዲሁም ተቋማዊ ተደራሽነቱን ማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራባቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቅሷል።

በተለይም በአስቸኳይ እና ወቅታዊ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታዎች ላይ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ተቋማዊ አወቃቀር ማሻሻያ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል። ባለድርሻ አካላትን ይዞ የሚፈልገውን ተቋማዊ ተልዕኮ ለማሳካት ከመድረኩ የሚሰበሰቡት ግብዓቶች የወደፊቱን የኮሚሽኑን የትኩረት አቅጣጫዎች በትክክል ለመቅረጽ እጅግ ወሳኝ መሆናቸውም ተብራርቷል።

የኢሰመኮ ያለፉት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ አፈጻጸም፣ ተልዕኮውን ሊያግዙ ወይም ተግዳሮት ሊሆኑ የሚችሉ ዐውዶች እንዲሁም ውስጣዊ አቅሞችን የዳሰሱ ሐሳቦች ቀርበዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎችም ኢሰመኮ በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ትኩረት ቢያደርግባቸው ያሏቸውን ሐሳቦች ሰጥተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ እውነቱ አለነ፤ መድረኩ ኢሰመኮ ያለፉት 5 ዓመታት ስኬቶቹን እና ክፍተቶቹን በገለልተኛ አካል አስጠንቶ ያቀረበበት፤ ባለድርሻ አካላትም ወሳኝ ግብዓቶች የሰጡበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፤ የቀጣይ 5 ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ ሰብአዊ መብቶች የማስፋፋት፣ የማስጠበቅ እና የማስከበር ዐቅም ይበልጥ እንዲጠናከር የዲጂታል አሠራርንና የፈጣን መረጃ ልውውጥ ሥርዓቶችን ማዕከል ያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል። አክለውም “ዕቅዱ ስኬታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ሚና አስፈላጊ ነው፤ ከተሳታፊዎች የተሰበሰቡ ግብዓቶች ለዕቅዱ መሳካት ትልቅ ዐቅም የሚፈጥሩ ናቸው” ብለዋል።