የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ክልል በሚገኙ በ4 ማረሚያ ቤቶች፣ በ19 ፖሊስ ጣቢያዎች እና በ4 መደበኛ ባልሆኑ የተጠርጣሪዎች ማቆያዎች ላይ ባከናወነው የታራሚዎች እና የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክትትል ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 16 እና 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የጋምቤላ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ የዞን ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋምቤላ ቅርንጫፍ፣ በክልሉ የሚገኙ የፖሊስ መምሪያ እና ፖሊስ ጣቢያ አዛዦች እንዲሁም በዞን ደረጃ የሚገኙ የፍትሕ እና አስተዳደር አካላት የሥራ ኃላፊዎች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል።



በመድረኩ ኢሰመኮ በክልሉ ማረሚያ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎች እና መደበኛ ባልሆኑ ማቆያዎች ላይ ባካሄደው ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጓል። በክትትሉ ሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች በፍርድ ቤት የሚሰጡ ትዕዛዞችን ማክበራቸው፣ ተጠርጣሪዎች በሕግ ሥልጣን በተሰጣቸው አካላት ብቻ በቁጥጥር ሥር የሚውሉ መሆኑ፣ በአብዛኛው ፖሊስ ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎች ላይ የሚደረግ ፍተሻ በሕግ አግባብ የሚከናወን መሆኑ፣ በተወሰኑ ማረሚያ ቤቶች ያለውን የመኝታ ቁሳቁስ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የተሠሩ ሥራዎች መኖራቸው፣ በሁሉም ማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች በቤተሰቦቻቸው፣ በጠበቆቻቸው፣ በሃይማኖት አማካሪዎቻቸው እና በሌሎች አካላት የመጎብኘት መብታቸው መከበሩ፣ የእምነት ነጻነት መከበሩ፣ ወደ ማረሚያ ቤት መግባት የሌለባቸው የተጠርጣሪና የታራሚ ንብረቶች በአግባቡ ተመዝግበው መያዛችው በመልካም አፈጻጸም የተለዩ መሆናቸው ተጠቅሷል።

ሆኖም በአብዛኛው ማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች የማደሪያ ክፍሎች መጨናነቅ፣ ከፍተኛ የንጽሕና ጉድለት ያለባቸውና በቂ መኝታ ያልተሟላላቸው መሆናቸው፣ በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በተጠርጣሪዎችና የሕግ ታራሚዎች ላይ ድብደባዎች የሚፈጸሙ መሆኑ፣ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት አለመዘርጋቱ፣ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚደረግ የተለየ እንክብካቤና ድጋፍ አለመኖር፣ በማረሚያ ቤቶች ምግብ ተዘጋጅቶ የማይቀርብ መሆኑ፣ ታራሚዎች የምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶችን ለማግኘት የሚቸገሩ መሆኑ፣ ለታራሚዎች የሚሰጠው ገንዘብ (በቀን 75 ብር) ከወቅቱ የኑሮ ውድነት አንጻር በቂ አለመሆኑ፣ የማረሚያ ቤቶች በጀት ወቅቱን ጠብቆ የማይለቀቅ መሆኑ፣ ማረሚያ ቤቶች የሕክምና አገልግሎት እና የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት እንዲሁም ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አለመኖራቸው ክትትሉ በአሳሳቢ ሁኔታ የለያቸው ግኝቶች ናቸው፡፡

በተጨማሪም በፖሊስ ጣቢያዎችንና መደበኛ ባልሆኑ ማቆያዎች ውስጥ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር የሚውሉና በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የማይቀርቡ መሆኑ፣ የጊዜ ቀጠሮ ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለተራዘመ ጊዜ በእስር እንዲቆዩ መደረጉ፣ ምግብ ሙሉ ለሙሉ የማይቀርብና ምግብ ማግኘት የሚቻልባቸው ስፍራዎች በቅርበት አለመኖር፣ ተጠርጣሪዎች ሕክምና የማያገኙ መሆኑ፣ እንዲሁም በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች የውሃ አቅርቦትና የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት አለመኖሩ ትኩረት የሚሹ መሆናቸው በክትትሉ ሪፖርት ተነስቷል፡፡


የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢሰመኮ ያቀረባቸውን ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች የሚቀበሏቸው መሆኑን በመግለጽ ኢሰመኮ የሚያደርጋቸውን የክትትልና ውትወታ ሥራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። የተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች የሰብአዊ
መብቶች አያያዝ ከፍተኛ ትኩረትን የሚፈልግ እና የሁሉንም አካላት በቅንጅት መሥራት የሚሻ መሆኑን የገለጹት ተሳታፊዎች ለተለዩት አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች መፍትሔ ለመስጠት ከክልሉ አስፈጻሚ አካላት ጋር በቅርበት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ዮናስ ሙሉጌታ፣ በክልሉ የተስተዋለው የተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች አያያዝ ሁኔታ እንዲሻሻል ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። አክለውም በክትትሉ የተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች መፍትሔ ማግኘት እንዲችሉ ኢሰመኮ በክልሉ ከሚገኙ የፍትሕ እና አስፈጻሚ አካላት ጋር የሚያደርገውን የውትወታ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡