የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰብአዊ መብቶች መሠረት ያደረገ አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ በኮሚሽኑ የቅብብሎሽ ሂደት ለሚሳተፉ አገልግሎት ሰጪ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ሰኔ 17 እና 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል። በመድረኩ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የተለያዩ የሲቪል እና የሙያ ማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል።





በመድረኩ ስለ ኢሰመኮ ሥልጣንና ተግባር፣ ስለሰብአዊ መብቶች፣ የሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ እሴቶችና መርሖች እንዲሁም የኢሰመኮ የቅብብሎሽ አሠራር ላይ ያተኮረ ገለጻና ማብራርያ ተሰጥቷል። በተጨማሪም ለተጎጂዎች ቀልጣፋ የድጋፍ አሰጣጥ ሥርዓት ለመተግበርና ከተቋማቱ ጋር ያለውን የቅብብሎሽና ትስስር ግንኙነት መደበኛ ለማድረግ ታልሞ በተዘጋጀው ረቂቅ የመግባቢያ ሰነድ ላይ ውይይት ተደርጓል። ሰነዱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የተፈጸመባቸው ተጎጅዎች ለኢሰመኮ አቤቱታቸውን ካቀረቡ በኋላ ነጻ የሕግ ድጋፍ፤ የመጠለያ፣ የጤና፣ የማኅበራዊና የሥነልቦና አገልግሎት በመስጠት ድጋፍ የሚያገኙበትን አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።




በተጨማሪም የቅብብሎሽ ሥርዓቱ ላይ ሊሟሉ ስለሚገቡ የአሠራር እና የመረጃ ጥበቃ መመሪያዎች፣ ልዩ ልዩ ቅጾች፣ የአገልግሎት ጥራት መቆጣጠሪያና የክትትል መለኪያዎች፣ እንዲሁም ለሠራተኞችና ለተባባሪ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የዐቅም ግንባታ ስልጠና የመስጠት አስፈላጊነት ላይ ውይይት ተደርጓል።




ተሳታፊዎች ከዚህ በፊት በቅብብሎሽ በሚሠሩበት ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ዋና ዋና ተግዳሮቶች አንስተው ከኢሰመኮ ጋር በሚተገበረው መደበኛ የቅብብሎሽ ሥርዓት አማካኝነት ሰብአዊ መብቶችን ያማከለ አገልግሎት ለመስጠት ስምምነታቸውን ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሚዛኔ አባተ (ዶ/ር) የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የፍትሕ አካላት እና የመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት ለተጎጂዎች የፍትሕ አሰጣጥ እና ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። በተጨማሪም እስካሁን ሲተገበር የነበረው የአጋርነትና የቅብብሎሽ አሠራር የተገልጋዮችን ፍላጎት ለማሳካት አስቸጋሪ እንደነበር ጠቅሰው ኢሰመኮ የጀመረው መደበኛ የቅብብሎሽ ሥርዓት ተገቢና ወቅታዊ በመሆኑ ለተጎጂዎች አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ሰብአዊ መብቶችን ያማከለ አገልግሎት እንዲሰጡ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።