የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች የውይይት መድረክ ሰኔ 25 እና 26 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል። በመድረኩ የኢሰመኮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከ45 በላይ የሚሆኑ በብሔራዊ እና በክልሎች የተቋቋመው የትብብር መድረኩ አባላት እና የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል።





በውይይቱ በሀገሪቱ የሰብአዊ መብቶች አጠቃላይ ሁኔታዎች እንዲሁም በትብብር መድረኩ የጋራ ሥራዎች ላይ ምክክር ተደርጓል። በተለይም በ2018 በጀት ዓመት በሲቪልና በፖለቲካ እንዲሁም በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ዙሪያ የተመዘገቡ ጉልህ እመርታዎችና ዋና ዋና ክስተቶች ተዳስሰዋል። በዚህም በሕይወት የመኖር እና በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቶች፣ በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች አያያዝ እንዲሁም ለጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች (የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች፣ ሴቶች እና ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን) መብቶች ጥበቃ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በተጨማሪም ሀገራዊ ምክክር፣ ምርጫ እና የሽግግር ፍትሕን በመሳሰሉ ሀገራዊ ሂደቶች ላይ የተስተዋሉ አበይት ጉዳዮች ተገምግመዋል።






በሌላ በኩል፣ ተሳታፊዎቹ የሲቪክ ምኅዳሩን አጠቃላይ ገጽታ እና በሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾችና በጋዜጠኞች ላይ እያጋጠሙ ባሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ መክረዋል። በዚህም በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የተቋቋሙ የትብብር መድረኮችን አፈጻጸም በመገምገም በአካባቢዎቹ ያለውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ክፍተቶችን ለይተዋል። የሰብአዊ መብቶች መከበርን ለማረጋገጥ በኢሰመኮ እና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር፣ ወጥ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም በመናበብ እና በቅንጅት መሥራት ወሳኝ አጽንኦት ተሰጥቶታል።





መድረኩ በተለይም በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች የሚገኙና የኢሰመኮ-ሲቪል ማኅበራት የትብብር መድረክ አባል የሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እርስ በእርስ የሚማማሩበት፣ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት እና ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ የሚሠሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ዕድል የፈጠረ ሲሆን በክልሎቹ የሚስተዋሉ ወቅታዊ እና አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎችን ለመፍታት በቀጣይ መወሰድ ያለባቸውን ስትራቴጂክ እርምጃዎች ለመለየት አስችሏል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ጆሴፍ ኑባድም የኢሰመኮ እና የሲቪል ማኅበራት ትብብር መድረክ ለሌሎች ተቋማዊ አጋርነቶች እንደ አርአያ ሊወሰድ የሚችል መሆኑን ገልጸው በተቋማት መካከል የሚደረግ የጋራ ጥረት ለሰብአዊ መብቶች መከበር የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፣ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን ለማሻሻል ወቅታዊ መረጃዎችን በመለዋወጥ፣ ጥረቶችን በማቀናጀት እና በመከታተል በጋራ መሥራት እንደሚገባ አስረድተዋል። አክለውም የትብብር መድረኩ አባላት ሰብአዊ መብቶች እንዲስፋፉ፣ እንዲጠበቁና እንዲከበሩ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።