ፖዶኮኒዮሲስ (podoconiosis) ምንድን ነው?
በአንዳንድ አካባቢዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ በተለምዶ “ዝሆኔ” ተብሎ የሚጠራው (ከዚህ በኋላ ፖዶኮኒዮሲስ) ትኩረት ከተነፈጋቸው የሐሩራማ/ሞቃታማ አካባቢ በሽታዎች (Neglected Tropical Disease) መካከል አንዱ ነው።1 በሽታው አብዛኛውን ጊዜ በሁለቱም የታችኛው የእግር ክፍሎች ላይ ወጥ ያልሆነ እብጠት የሚያስከትል ሲሆን፤ ትክክለኛ መንስኤው በእርግጠኛነት ተለይቶ የሚታወቅ ባይሆንም በእሳተ ገሞራ ከሚፈጠር ቀይ የሸክላ አፈር ጋር ለረጅም ጊዜ በሚኖር ንክኪ (long-term contact with volcanic red clay soils) እንደሚከሰት መረጃዎች ያመላክታሉ።2
በዓለም አቀፍ ደረጃ 4 ሚሊዮን የፖዶኮኒዮሲስ ታማሚዎች እንዳሉ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ በአፍሪካ፣ በማዕከላዊና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በደቡብ ምሥራቅ እስያ በሚገኙ ሞቃታማ አካባቢዎች እንደሚገኙ ይገመታል።3 በኢትዮጵያም የፖዶኮኒዮሲስ በሽታ ከፍተኛ ስርጭት ያለ ሲሆን፤ በተለይም ከ345 በላይ በሆኑ ወረዳዎች ውስጥ በስፋት/ተደጋጋሚ በሆነ መልኩ (endemic) ይከሰታል።4 በሀገሪቱ ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ የፖዶኮኒዮሲስ ታማሚዎች መኖራቸውንና ከአጠቃላዩ ሕዝብ ከ34.9 እስከ 43.8 በመቶ የሚሆነው ለበሽታው መከሰት አመቺ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚኖር ጥናቶች ያመላክታሉ5።
ፖዶኮኒዮሲስ የሚያስከትላቸው የሰብአዊ መብቶች ተጽዕኖዎች ምንድን ናቸው?
የፖዶኮኒዮሲስ በሽታ ያለባቸው ሰዎች በታችኛው የእግር ክፍላቸው ላይ በሚፈጠር እብጠት ሕመም እና ምቾት ማጣት ሳቢያ ለረጅም ጊዜ መቆም ወይም መራመድ ስለማይችሉ ብዙውን ጊዜ አካላዊ ውስንነቶች ያጋጥሟቸዋል። ይህም ሁኔታ የሥራ አቅማቸው እንዲቀንስ እና ከሥራ በተደጋጋሚ እንዲቀሩ የሚያደርግ በመሆኑ፣ በሽታው ያለባቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ለከፋ የኢኮኖሚ ችግር፣ ለኑሮ ዋስትና ማጣት እንዲሁም ለምግብ እና ለአካላዊ ድጋፍ በቤተሰብ አባላት ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋል። በአጠቃላይ በሽታው የትምህርት እና የሥራ እድሎች ላይ እንቅፋት በመሆን በታማሚዎች ላይ ከባድ ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ያስከትላል።
ፖዶኮኒዮሲስ መከላከል የሚቻል ተላላፊ ያልሆነ በሽታ ቢሆንም፣ ስለ በሽታው ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ ስለ መንስኤው፣ መከላከያ ዘዴዎቹ እና ሕክምናው በማኅበረሰቡ ዘንድ የተሳሳቱ አመለካከቶች በሰፊው ይስተዋላሉ። በዚህም ምክንያት በበሽታው የተጠቁ ግለሰቦች ከማኅበረሰቡ አባላት እና አልፎ አልፎም ከጤና ባለሙያዎች ከፍተኛ መገለል ይደርስባቸዋል።6 በተለይም እንደ ሰርግ እና ለቅሶ ባሉ የማኅበራዊ ሕይወት እንቅስቃሴዎች እንዳይሳተፉ፣ ትዳር መመስረት እንዳይችሉ እንዲሁም የአመራር እና የውሳኔ ሰጪነት ሚናዎችን እንዳያገኙ ይደረጋሉ።
ይህ ዓይነቱ መገለል እና አድልዎ በታማሚዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች እና የዕለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታ እንዲሁም የወደፊት ዕድሎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። ለአብነትም በፖዶኮኒዮሲስ የተጠቁ ሕፃናት በእኩዮቻቸው እና በተቋም ደረጃ ባለ መዋቅራዊ አድልዎ እና መገለል ሳቢያ ከትምህርታቸው ሲገለሉ፤ በሕግ ዕውቅና ያለው የመማር መብታቸው ይጣሳል፤ ይህም ወደፊት በሥራ የመቀጠር ዕድላቸውን እና የሕይወት ደረጃቸውን የማሻሻል አቅማቸውን በእጅጉ ይገድባል። በተመሳሳይ ሁኔታም መሰል ማኅበራዊ መገለሎች ታማሚዎች በንግድና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እኩል ተሳትፎ የማድረግ አቅማቸውን በመገደብ የሥራ እና የኑሮ ሁኔታቸውን በዘላቂነት የማሻሻል መብታቸውን እንዲጣስና ለድህነት እንዲጋለጡ ያደርጋል።
በአጠቃላይ፣ በፖዶኮኒዮሲስ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ትምህርት ቤቶችን፣ የሃይማኖት ተቋማትን እና የገበያ ቦታዎችን ጨምሮ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ የማግለልና የአድልዎ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል።
በማኅበረሰቡ ዘንድ ከሚስተዋሉ የተለመዱ የማግለል ዓይነቶችና መገለጫዎች መካከል፦
- በበሽታው ከተጠቁ ግለሰቦች ወይም ከቤተሰቦቻቸው አባላት ጋር ጋብቻ ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆን እንዲሁም የትዳር አጋር በበሽታው ከተያዘ/ች ፍቺ መፈጸም፤
- ሆነ ብሎ መራቅ እና አካላዊ ንክኪ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆን፤
- በበሽታው የተጠቁ ሰዎችን እና የቤተሰብ አባላትን ከማኅበራዊ ዝግጅቶች ማግለል፤
- በበሽታው የተጠቁ ሰዎች አጠገብ ሲያልፉ አፍንጫን መሸፈን እና ሌሎች መሰል ስብእንና/ክብርን የሚነኩ ምልክቶችን መጠቀም፤
- በትምህርት ቤት የክፍል ጓደኞች አብረው ለመቀመጥ ፈቃደኛ አለመሆን፤
- ሌሎች የቤተሰብ አባላት በበሽታው የተጠቁ የቤተሰብ አባላትን ለመቅረብ አለመፍቀድ፤ እንዲሁም
- በበሽታው በተጠቁ ግለሰቦች የሚሸጡ እቃዎችን አለመግዛት የሚሉት ይገኙበታል።
በእነዚህ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ተንሰራፍተው በሚገኙ ሌሎች መሰል የአድልዎ እና የማግለል ተግባራት የተነሳ በፖዶኮኒዮሲስ የተጠቁ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ከማኅበረሰብ ሕይወት ራሳቸውን በማግለል ብቸኝነትን ይመርጣሉ። በተጨማሪም እነዚህ የአድልዎ እና የማግለል አመለካከቶች ዝቅተኛ በራስ መተማመን፣ ሥነ-ልቦናዊ ጭንቀት እና ራስን ለመቀበል (self-acceptance) መቸገርን ጨምሮ ለአእምሮ ጤና እክሎች ያጋልጣሉ። ይህም የበሽታውን ማኅበራዊ ጫና ከማባባስ ባለፈ ታማሚዎች በተገቢው ጊዜ የጤና እርዳታ እንዳይሹ እና ክትትል እንዳያደርጉ በማድረግ አጠቃላይ የጤና ሁኔታ እና የኑሮ ደረጃ መቀነስን ያስከትላሉ።
በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት በመሥራት፣ የፖዶኮኒዮሲስ ታማሚዎችን ለመደገፍ ሕመሙን ትኩረት ከተነፈጓቸው የሐሩራማ/ሞቃታማ አካባቢ በሽታዎች አጠቃላይ አጀንዳ ውስጥ በማካተት አበረታች እርምጃዎችን ወስዷል። በተለይም በሦስተኛው ብሔራዊ የጤና ስትራቴጂክ ዕቅድ (እ.ኤ.አ 2021–2025) በሽታው በስፋት በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ሥርጭቱን ለመቆጣጠርና ብሎም ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። በዕቅዱ የተካተቱ እርምጃዎች ለበሽታው ሕክምና የማኅበረ ሥነ-ልቦና ድጋፍ ለመስጠት፣ ማኅበራዊ መገለልን ለመቀነስ እንዲሁም የባሕሪ ለውጥን ለማምጣት ያለሙ ናቸው። እነዚህ ጥረቶች ከጤና ጥበቃ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እና ከዓለም ጤና ድርጅት ፍኖተ ካርታ (እ.ኤ.አ. 2021–2030) ጋር የተጣጣሙ ናቸው።
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ራቅ ባሉ የገጠር አካባቢዎች የእግር ንጽሕና አጠባበቅን፣ የቁስል እንክብካቤን፣ የጫማ አቅርቦትን እና የጤና ትምህርትን ጨምሮ ማኅበረሰቡን መሠረት ያደረጉ እንክብካቤዎችን በማስጀመር እና በማቅረብ ረገድ የላቀ ሚና ተጫውተዋል። በተለይም አንዳንድ ድርጅቶች ማኅበራዊ አድልዎን እና ስለ በሽታው ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል የሥነ-ልቦና ማጠናከሪያ ድጋፎችን እና የማኅበረሰብ ግንዛቤ ማስጨበጫ መርኃ-ግብሮችን አስተዋውቀዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ አበረታች ጅማሮዎች አሁንም ወጥነት የሚጎድላቸው፣ የተደራሽነት ውስንነት ያለባቸው እና በከፍተኛ ደረጃ በውጪ የገንዘብ ድጋፎች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በተጨማሪም ከቁሳቁስ አቅርቦት፣ ከሰለጠነ የሰው ኃይል እና በመጀመሪያ የጤና እንክብካቤ ማዕከላት ተገኚ ከመሆን አኳያ ክፍተቶች ይታዩባቸዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ያለውን የፖዶኮኒዮሲስ ጫናን ይበልጥ ለመቀነስ፣ መንግሥት ሙሉ በሙሉ አዳዲስ አሠራሮችን ከመዘርጋት ይልቅ ነባር እና ለአተገባበር ምቹ የሆኑ እርምጃዎችን ማጠናከር እና ማስፋፋትን ቅድሚያ በመስጠት ሊሠራ ይገባል። መንግሥት ዓለም አቀፍና ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ግዴታዎቹን ለመወጣት በተገኝነት፣ ተደራሽነት፣ ተቀባይነት እና ጥራት ማዕቀፍ (Availability, Accessibility, Acceptability, and Quality framework) እየተመራ የፖዶኮኒዮሲስ ሕክምናና እንክብካቤ አገልግሎትን በብሔራዊ የጤና ሥርዓት ውስጥ በተቀናጀ ሁኔታ ማካተት ይኖርበታል። ይህም በአንድ በኩል የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎትን በመጠቀም እንደ ሳሙና፣ ቅባት እና ልዩ ጫማዎች ያሉ መሠረታዊ አቅርቦቶች መገኘታቸውን ማረጋገጥን የሚጠይቅ ሲሆን፤ በሌላ በኩል በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ከቦታ እና ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችን ለማስወገድ፣ ሕክምናውን በጤና ጣቢያዎች እና ጤና ኬላዎች ተደራሽ ማድረግን ይጠይቃል። ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት በጤና ተቋማት ውስጥ የሚስተዋለውን ተቋማዊ ማግለል/አድልዎ ለማስወገድ ሙያዊ የሕክምና ሥልጠናን ከማስፋፋት ጎን ለጎን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ጎጂ የሆኑ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን በማሰማራት የአገልግሎቱን ተቀባይነት እና ጥራት ማረጋገጥ ይኖርበታል።
በተለይም በጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች አማካኝነት ስለ ሕመሙ የሚስተዋሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለመቅረፍ፣ ማኅበራዊ መገለል/አድልዎን ለመቀነስ እና በጊዜ የሕክምና ዕርዳታ የመፈለግ ልማድን ለማበረታታት፤ ተጨባጭ የሆኑና ማኅበረሰብን መሠረት ያደረጉ የጤና ትምህርት መርኃ-ግብሮች ሊጠናከሩ ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ በድጎማ የተደገፈ የወጪ ማስመለስ ሥርዓት (subsidized cost-recovery mechanism) ተግባራዊ ማድረግ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦች አገልግሎቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ለማድረግ እና ዘላቂነቱን ለማስቀጠል ያግዛል። በተጨማሪም ከውኃ፣ ከንጽሕና አጠባበቅ፣ ከቤት ልማት እና ከትምህርት ዘርፎች ጋር ጠንካራ የባለብዙ ዘርፍ ትብብር (Multisectoral Collaboration) መፍጠር፤ እንደ የተሻሻለ የመኖሪያ ቤት ወለል ንጣፍ፣ የጫማ አጠቃቀም እና የእግር ንጽሕና ያሉ የመከላከያ እርምጃዎች መተግበርን የሚያጠናክር ሲሆን፤ መንግሥት የጤና መሠረተ ልማትን በማጠናከር እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ያለውን አጋርነት በማስቀጠል፣ በኢትዮጵያ በበሽታው የሚያዙ አዳዲስ ሰዎችን ቁጥር መቀነስና ቀደም ሲል በበሽታው የተጎዱ ሰዎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ይቻላል።
[1] Kidus Meskele, Realizing the right to health of people living with Podoconiosis; Lessons from the field, PP 2
[2] Tekola Ayele F, Alemu G, Davey G, Ahrens C. Community-based survey of podoconiosis in Bedele Zuria woreda, west Ethiopia, PP 119.
[3] Muluken M, Yohannes K, et al, ‘Lived Experience of People living with podoconiosis in Southern Ethiopia: a phenomenological study’, 2025, PP 3
[4] Temesegn L, Amene, et al, ‘Stigma Related to Podoconiosis in Ethiopia; A Systematic Review’, PP 4
[5] Kebede D, Biruck K, ‘PODOCONIOSIS In Ethiopia: From Neglect to Priority Public health problem’, 2017, PP 65