የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ላይ የማኅበረሰቡን ንቁ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን በኦሮሚያ ክልል ለሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአዳማ፣ በድሬዳዋ እና በያቤሎ ከተሞች ሰጥቷል፡፡። ሥልጠናዎቹ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፣ አካታች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መስፈርቶችን ያሟላ እንዲሆን ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ አካላትን ዐቅም ለማጠናከር ያለመ ነው።


በአዳማ ከተማ ከጥቅምት 23 እስከ ጥቅምት 27 ቀን 2019 ዓ.ም. በተካሄደው ስልጠና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ 29 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል። ስልጠናው ተሳታፊዎች የሽግግር ፍትሕ ላይ ያላቸውን መረዳት እንዲጨምር ከማድረግ ባለፈ፤ ሂደቱ ሁሉንም ማኅበረሰብ የሚያሳትፍ፣ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፣ አካታች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን ያከበረ እንዲሆን ዐቅማቸውን የሚያጎለብት ግንዛቤ ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በሽግግር ፍትሕ አውድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የመከታተል፣ ሰንዶ የመያዝ እና የውትወታ ሥራን የመስራት ክህሎታቸውን ለማዳበር የሚረዱ የተግባር ልምምዶችን አድርገዋል፡፡


በተመሳሳይ ኢሰመኮ ይህንኑ በሰብአዊ መብቶች እና ሽግግር ፍትሕ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና ከሐረሪ ክልል ለተወጣጡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አባላት እና አመራሮች ከጥቅምት 30 ቀን 2019 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 4 ቀን 2019 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ አካሂዷል፡፡ በስልጠናው የአካል ጉዳተኞችን እና ኤች አይ ቪ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሰዎችን የሚወክሉ ማኅበራትን ጨምሮ ከተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት የተውጣጡ 35 ሰልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢሰመኮ ከቦረና ዞንና አቅራቢያ ወረዳዎች ለተውጣጡ የእምነት ተቋማት፣ የአባ ገዳ፣ የሃደ ሲንቄ አደረጃጀቶች እና ከባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለተውጣጡ የማኅበረሰብ መሪዎች በሰብአዊ መብቶች እና ሽግግር ፍትሕ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ከጥቅምት 30 እስከ ኅዳር 2 ቀን 2019 ዓ.ም. በያቤሎ ከተማ ሰጥቷል፡፡


በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ክላስተር የተካሄደውና 35 ተወካዮች የተሳተፉበት ይህ መድረክ፤ የማኅበረሰብ መሪዎች በሰብአዊ መብቶች ጥበቃና በሽግግር ፍትሕ ሂደት ያላቸውን ሚና ለማጠናከር ያለመ ነው። ተሳታፊዎቹ በሌሎች ሀገራት የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች ውስጥ የእምነት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የነበራቸውን ተሞክሮዎች በመዳሰስ፣ ሂደቱን በባለቤትነት ለመምራት የሚያስችል ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲጨብጡ አግዟል። ይህ ሥልጠና ከዚህ ቀደም በተለያዩ የጸጥታ ሁኔታዎች ምክንያት ተደራሽ ሊሆኑ ያልቻሉ የኦሮሚያ ክልል የማኅበረሰብ ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖር ዕድል ፈጥሯል።

ስልጠናውን አስመልክቶ መልእክት ያስተላለፉት የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ዳይሬክተር ዶ/ር መቅደስ ታደለ፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ሰብአዊ መብቶችን ያከበረ እና ተጎጂዎችን ያማከለ እንዲሆን የሲቪል ማኅበራት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው በማኅበረሰቡ ዘንድ ዕውቀት እና ግንዛቤ እንዲስፋፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በመሰነድ፤ ለተጎጂዎች የሥነ ልቦና እና የሕግ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም የሕግ እና የሥርዓት ማሻሻያዎች እንዲተገበሩ በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው አጽንዖት ሰጥተዋል።