የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሽግግር ፍትሕ ሂደት ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራትን መረጃ ለመለዋወጥ፣የጋራ እቅዶችን ለማውጣት እና በንዑስ ቡድኑ ዓመታዊ የድርጊት መርኃ ግብር መሠረት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የስልጠና ፍላጎት ለመገምገም ከኢሰመኮ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የትብብር መድረክ እና ከሽግግር ፍትሕ ንዑስ ቡድን አባላት ጋር መስከረም 20 ቀን 2019 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አድርገዋል። 

ውጤታማ የሲቪል ማኅበረሰብ ተሳትፎ ተአማኒ፣ አካታች እና ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ የሽግግር ፍትሕ ሂደት እንዲኖር ወሳኝ ድርሻ አለው። ይህ የሽግግር ፍትሕ ንዑስ ቡድንም የሲቪል ማኅበረሰብ አካላት መረጃ የሚያለዋውጡበት፣ የሥራ ቅንጅት የሚፈጥሩበት፣ የሥራ መደጋገምን የሚያስቀሩብት እና በሀገራዊ የሽግግር ፍትሕ ውይይቶች ላይ ጉልህ አስተዋጽፆ  የሚያበረክቱበት መድረክ ሆኖ ያገለግላል። በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን እውቀት፣ ክህሎት እና ስትራቴጂያዊ ዝግጁነትን ማጠናከር፡ የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት አሳታፊ እና በሰብአዊ መብቶች መርሖች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያረጋግጣል። 

በ2013 ዓ.ም. የተቋቋመው የኢሰመኮ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የትብብር መድረክ፣ በኢሰመኮ እና ኢትዮጵያ ውስጥ በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ በሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል ዘላቂ ውይይትና ትብብር እንዲኖር የሚያስችል ተቋማዊ መድረክ ነው። በኢሰመኮ እና በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ጥምረት በጋራ የሚመራው የትብብር መድረኩ ንዑስ ቡድን፣ በሽግግር ፍትሕ ሂደት ላይ የተሰማሩ ወይም ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸውን አካላት በአንድ ላይ ያሰባሰበ ሲሆን ይህም ጥረት ኢሰመኮ በሕግ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሠረት በተቋማት መካከል ቅንጅትን የመፍጠር እና በሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ስልቶች ውስጥ አካታችነትን የማረጋገጥ ተልዕኮዎን ለማጠናከር ያስችለዋል። 

መድረኩ ከዚህ ቀደም የነበረውን የአባላት ቁጥር ወደ 41 ማሳደግ መቻሉ እና በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ተቋማት በተጨማሪ ከአፋር፣ ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች የተወጣጡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዲካተቱ በማድረግ ውክልናውን ማስፋት ተችሏል። ይህም የጎላ ተሳትፎ በትብብር መድረኩ ላይ ያለው ተቋማዊ እምነት ማደጉን አመላካች ሲሆን የተለያዩ ክልላዊ ድምፆችና ዕይታዎችን ያካተተ የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ምህዳር በመቅረጽ ረገድ የሚኖራቸውን ዕድል ያሰፋዋል። 

በመድረኩ በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደትና ዋና ዋና ኩነቶች ላይ በባለሙያ ማብራሪያ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። አባላቱ በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የሚያከናውኗቸውንና በቀጣይም ያቀዷቸውን ተግባራት አቅርበዋል። ይህም መድረኩ የጋራ መርኃ ግብሮችን እንዲያዘጋጅ አግዟል። በተጨማሪም ተሳታፊዎች የንዑስ ቡድኑን የ2019 በጀት ዓመት የጋራ የድርጊት መርኃ ግብር እና የትግበራ ጊዜ ሰሌዳ በጋራ ነድፈዋል። 

ከውይይቱ ዋና ትኩረቶች መካከል ኢሰመኮ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያዘጋጀው ልዩ የሽግግር ፍትሕ የስልጠና ማኑዋል ማቅረብ ነበር። ተሳታፊዎች የስልጠና ማኑዋሉን ይዘት፣ ዘዴ እና አግባብነት ለመገምገም በተዋቀረ የቡድን ውይይት ተሳትፈዋል። በዚህ የፍላጎት ዳሰሳ የተሰበሰቡ አስተያየቶች ማኑዋሉን ለማበልጸግ እና በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን አዳዲስና ወቅታዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ያገናዘቡ ቀጣይነት ያላቸው የዐቅም ማሳደጊያ መርኃ ግብሮችን ለማዘጋጀት ግብአት ይሆናሉ።