የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ 
ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያዩ ፖሊስ መምሪያዎች በእስር ላይ ያሉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባሎች የእስር ሁኔታን በተመለከተ ለረጅም ጊዜ ሲያደርገው ከነበረው ክትትል በተጨማሪ ከፓርቲው እና ከእስረኞች ቤተሰቦች በቀረቡ አቤቱታዎች መነሻነት ከመጋቢት 1 እስከ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. በቡራዩ ከተማ፣ በገላን ከተማ እና በሰበታ ፖሊስ መምሪያዎች በአካል በመገኘት ክትትል በማድረግ እስረኞችን፣ የፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎችን፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንን እና የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተወካዮችን በማነጋገር ምርመራ አድርጓል። በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት እስረኞቹን በሚመለከት በፍርድ ቤት እና በዐቃቤ ሕግ የተሰጡ ውሳኔዎችን እና ትዕዛዞችን እንዲሁም የሕክምና ሰነዶችን ተመልክቷል፡፡

በቡራዩ ፖሊስ መምሪያ በእስር ላይ የነበሩ አቶ ሚካኤል ጎበና፣ አቶ ኬኔሳ አያና፣ ዶ/ር ገዳ ወልጅራ፣ አቶ ዳዊት አብደታ፣ አቶ ለሚ ቤኛ፣ አቶ ገዳ ገቢሳ የተባሉ የፓርቲው አመራር መሆናቸውን የገለጹ ስድስት እስረኞችን ኮሚሽኑ አነጋግሯል። በተጨማሪም ኮሎኔል ገመቹ አያና በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል፣ እንዲሁም አቶ አብዲ ረጋሳ ገላን ከተማ በሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ካምፕ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ መሆኑን ከቤተሰብ እና ከጠበቆቻቸው መረዳት ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ አቶ በቴ ኡርጌሳ በእስር ላይ እያሉ ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት በፖሊስ ዋስትና ተፈቅዶላቸው በአንድ የሕክምና ተቋም ሕክምና ላይ የነበሩ መሆኑን ኮሚሽኑ ተመልክቷል፡፡ 

በዚህ ምርመራ መሰረት፣ ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቁ የፈቀደላቸው፣ የክስ መዝገቦቻቸው ተዘግተው በፍርድ ቤት ውሳኔ በነፃ የተሰናበቱ፣ ምንም አይነት ክስ ያልተመሰረተባቸው እና ዐቃቤ ሕግ ክስ የማይመሰርትባቸው መሆኑን በማረጋገጥ የምርመራ መዝገባቸው የተዘጋ፤ ሆኖም ከወራት እስከ 2 ዓመት ለሚሆን ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ከሕግ አግባብ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙና የተወሰኑትም በእስሩ ሂደት በተፈጸመ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እና ድብደባ ለተለያዩ የአካል ጉዳቶችና የጤና እክል የተጋለጡ እስረኞች መሆናቸውን ኢሰመኮ ተረድቷል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የኦነግ ፓርቲ አመራሮች ለተራዘመ ጊዜ ከሕግ አግባብ ውጭ ታስረው የሚገኙ በመሆኑ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቁ እና ለደረሰባችው ጉዳት ሊካሱ የሚገባ ሲሆን፤ በተጨማሪም የፍርድ ቤትና የዐቃቤ ሕግ ውሳኔዎች በተደጋጋሚ እየተጣሰ እስረኞቹ ከሕግ ውጪ ለተራዘመ እስር መዳረጋቸው ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ስለሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አፋጣኝ ማጣራት አካሂዶ ተገቢውን እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል” ብለዋል፡፡

የኢሰመኮ የሲቪል፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጂብሪል በበኩላቸው “በተለይም ታሳሪዎቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በመሆናቸው በሕዝባዊ አገልግሎት ስራቸው ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይጋለጡ ጥበቃ ሊደረግ ሲገባ፤ በተግባር የተገላቢጦሽ መሆኑ አሳዛኝ መሆኑን አስታውሰው ጉዳዩ አፋጣኝ እልባት ያስፈልገዋል” ሲሉ አሳስበዋል።


ስለ ጉዳዩ ዝርዝር መረጃዎች፣ የክትትሉን ሂደት እና ግኝቶች ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ፓርቲ አባላት የሆኑ እስረኞች 
በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ ፖሊስ መምሪያ በእስር ላይ ያሉ አቶ ሚካኤል ጎበና፣ አቶ ኬኔሳ አያና፣ ዶ/ር ገዳ ወልጅራ፣ አቶ ዳዊት አብደታ፣ አቶ ለሚ ቤኛ፣ አቶ ገዳ ገቢሳ የተባሉ የኦነግ ፓርቲ አመራር መሆናቸውን የገለጹ ስድስት እሰረኞችን ኮሚሽኑ አነጋግሯል፡፡ በተጨማሪም ኮሎኔል ገመቹ አያና እና አቶ አብዲ ረጋሳ በቅደም ተከተል በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል እና ገላን ከተማ በሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ካምፕ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ መሆኑን ከቤተሰብ እና ከጠበቆቻቸው መረዳት ተችሏል፡፡ አቶ በቴ ኡርጌሳ በእስር ላይ እያሉ ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በፖሊሰ ዋስትና ተፈቅዶላቸው በአንድ የግል የሕክምና ተቋም ሕክምና ላይ የነበሩ መሆኑን ኮሚሽኑ ተመልክቷል፡፡

አቶ ለሚ ቤኛ እና አቶ ዳዊት አብደታ ሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር ውለው በምርመራ ላይ ከቆዩ በኋላ፣ በኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በተመሰረተባቸው የወንጀል ክስ በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 328156 ጉዳያቸው ታይቶ ፍርድ ቤቱ በታኅሣሥ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በነጻ አሰናብቷቸዋል፡፡ የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወ/ይ/መ/ቁጥር 201403 ይግባኙን ተመልክቶ ሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ አጽንቷል፡፡ በዚህ መሰረት ሁለቱም ተከሳሾች ከእስር እንዲለቀቁ እና ለዋስትና አስይዘውት የነበረው ገንዘብ እንዲመለስላቸው ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተሰጠ ቢሆንም፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አልፈጸመም፣ ታሳሪዎቹም ከእስር አልተለቀቁም። አቶ ለሚና አቶ ዳዊት ከ12 ጊዜ በላይ ከአንድ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ሌላ ፖሊስ ጣቢያ እና በሌሎች ኢ-መደበኛ የእስር ቦታዎች እንደተዘዋወሩና አሁንም ያለምንም ሕጋዊ ሂደት በእስር ላይ የሚገኙ መሆኑን ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡

አቶ ሚካኤል ጎበና እና አቶ ኬኒሳ አያና ሰኔ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ፣ የወንጀል ምርመራ ሲካሄድባቸው ቆይተው ጳጉሜ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. የቡራዩ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቁ የወሰነ ቢሆንም የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አልተፈጸመም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ታኅሣሥ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በዐቃቤ ሕግ መዝገብ ቁጥር 01/25051 በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ ለመመስረት የሚያስችል በቂ ማስረጃ ያላገኘ መሆኑን በመጥቀስ ተጠርጣሪዎቹ ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ መስጠቱን መረዳት ተችሏል፡፡ ይሁንና በፍርድ ቤቱም ሆነ በዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት የተሰጡት ሁለቱም ትዕዛዞች ያልተፈጸሙ ሲሆን፣ እስረኞቹ ከቡራዩ ፖሊስ መምሪያ ወደ ገላን ፖሊስ መምሪያ ተዘዋውረዋል። አቶ ሚካኤል እና አቶ ኬኒሳ ወደ ገላን አካባቢ ከተዛወሩ በኋላ ለገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ተጨማሪ አቤቱታ የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በመዝገብ ቁጥር 06250 በዋስትና እንዲለቀቁ የወሰነ ቢሆንም፣ አሁንም የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሳይፈጽም በመቅረቱ ሁለቱም ታሳሪዎች ከሕግ ውጭ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

ዶ/ር ገዳ ወልጅራ ታኅሣሥ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተይዘው በቡራዩ ፖሊስ መምሪያ እንደታሰሩ ገልጸው፣ አንድ ቀን ለጊዜ ቀጠሮ ቡራዩ ከተማ በሚገኘው ወረዳ ፍርድ ቤት ከመወሰዳቸው በቀር በድጋሚ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ቤተሰብ ለማግኘት እንዳልተፈቀደላቸውና፣ ከአንድ እስር ቤት ወደ ሌላ እስር ቤት በመዘዋወር እስከ ቦረና ዞን ፖሊስ መምሪያ ድረስ ተወስደው እንደነበርና “በበላይ አመራር ትዕዛዝ” በሚል ታስረው እንደሚገኙ ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡ 

አቶ ገዳ ገቢሳ የካቲት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. በቡራዩ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ታስረው የሚገኙትንና የኦነግ አመራር የነበሩት አቶ አብዲ ረጋሳን ለመጠየቅ በሄዱበት በኦሮሚያ ፖሊስ ተይዘው እንደታሰሩ ገልጸው፤ የቡራዩ ወረዳ ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቁ ወስኖ የነበረ ቢሆንም የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ካለመፈጸሙም በላይ ታሳሪውን ወደ ተለያዩ የእስር ቦታዎች (ቡራዩ፣ ገላን፣ አዋሽ መልካሳ ጊዜያዊ እስር ስፍራ እና እስከ ቦረና ዞን ፖሊስ መምሪያ ድረስ) በማዘዋወር እስከ አሁን ድረስ ከሕግ ውጪ በእስር ላይ እንደሆኑ ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡

በዚህ የምርመራ ሪፖርት ከተጎበኙት እስረኞች መካከል አንዱ ታሳሪ ያለፉበትን ሁኔታ ለኢሰመኮ ሲያስረዱ “ቡራዩ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 03 ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ የኦነግ አመራሮችን ለመጠየቅ በሄድኩበት ይዘው አሰሩኝ፣ ቡራዩ ወረዳ ፍርድ ቤት አቀረቡኝ ፤ ፍርድ ቤቱም 10 የምርመራ ቀናት ለፖሊስ ፈቀደ፣ ከ10 ቀናት በኋላ ድጋሚ ፍርድ ቤት ቀረብኩ፤ፍርድ ቤቱን ዋስትና ጠየቅኩኝ፣ ፖሊስም አልተቃወመም ነበር፣ በአምስት ሺህ ብር ዋስትና እንድለቀቅ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጠልኝ፣ ቤተሰቦቼ የዋስትና ገንዘቡን ከፍለው ሲመጡ አንድ የቡራዩ ከተማ ወረዳ 03 ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ “እሱ በበላይ አካል ስለሚፈለግ አይለቀቅም፤ ከዚህ የማትሄዱ ከሆነ እናንተንም አስራችኋለሁ” በማለት አስፈራራቸው፣ ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤት ሳልቀርብ እና ለምን እንደታሰርኩም ሳይነገረኝ “የበላይ አካል ነው የፈለገህ ለዚያ ነው የታሰርከው” እያሉኝ እስከ አሁን በተለያዩ ቦታዎች እያዘዋወሩኝ በእስር እገኛለሁ ” በማለት አስረድተዋል። 

የእስረኞች አያያዝ ሁኔታ
ኮሚሽኑ በምርመራው ወቅት ያነጋገራቸው እስረኞች በተያዙበት ጊዜ፣ በፖሊስ ምርመራ ወቅት እንዲሁም በተለያዩ የእስር ቤቶች ቆይታ ጊዜያቸው በተፈጸመባቸው ድብደባ፣ በእስር ቦታ መጣበብ እና የንጽሕና ጉድለት፣ በምግብ እጥረት፣ በሕክምና እጦት፣ እና በሚደርስባቸው የሥነ ልቦና ጫና ምክንያት ለሕመም መጋለጣቸውንና የአካል ጉዳትም እንደደረሰባቸው ለኮሚሽኑ ገልጸዋል። 

ከእስረኞቹ አንዱ ግንቦት 2013 ዓ.ም. በአዋሽ መልካሳ ጊዜያዊ እስር ቤት ውስጥ በተፈጸመባቸው ድብደባ ሦስት ቦታ ጭንቅላታቸው ላይ እንደተፈነከቱ፣ እግራቸው ላይም ጉዳት እንደደረሰበት ለምርመራ ቡድኑ ገልጸዋል፡፡ 

ሌላኛው እስረኛ የደረሰባቸውን ሁኔታ ለኢሰመኮ ሲያስረዱ “ከመጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በቡራዩ ፖሊስ መምሪያ ታስሬ በነበረበት ወቅት የኩላሊት ሕመም ስለነበረብኝ መጸዳጃ ቤት በተደጋጋሚ መሄድ ያስፈልገኝ ነበር፣ ሆኖም ፖሊሶች ለመሄድ በጠየቅኩ ጊዜ አይወስዱኝም ነበር፤ ቀን ላይ ቢሆንም ከእስር ክፍል መውጣት አይቻልም፡፡ በዚህ የተነሳ የኩላሊት ሕመሜ ጸናብኝ፣ ሕክምና አላገኘሁም፡፡ ማደሪያ ክፍሎቹ የተጨናነቁ ስለነበር እና የአስም ሕመምም ስላለብኝ እቸገራለሁ፣ ቤተሰቦቼን ፖሊሶቹ ያመናጭቋቸዋል፣ ከጠበቃ ጋር እንድገናኝ አይፈቀድልኝም፣ ፖሊሶቹ ለምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ሁሉ ‹‹እናንተ የእኛ እስረኛ አይደላችሁም፤ ለበላይ አካል ጥያቄያችሁን እናቀርባለን›› ይሉናል፣ ሕክምና እንዲወስዱኝ ስጠይቃቸው ‹‹የበላይ አካል አልፈቀደም›› ብለው ስለከለከሉኝ ሕመሜ የከፋ ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡” በማለት አስረድተዋል። 

አንድ ሌላ እስረኛም ያለፉበትን ሂደት ለኮሚሽኑ ሲያስረዱ “ቅዳሜ ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. የኦሮሚያ ፖሊስ 126 ሰዎችን ከአዋሽ መልካሳ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ አያማ የዶሮ እርባታ ግቢ ወስደው አስገቡን፡፡ አዋሽ መልካሳ ለ2 ወራት ታስረን ስንቆይ ቤተሰቦቻችን የት እንዳለን አያውቁም ነበር፡፡ እዛ እያለን ቁርስ አንድ ዳቦና ሻይ ሲሆን ምሳና እራት ደግሞ ሽሮና ዳቦ ነበር የሚቀርብልን፡፡ የውሃ ችግር ስላለ ለ5 ቀናት ውሃ ሳናገኝ የቆየንበት ጊዜ ነበር። ለመጠጥ የሚሆን ውሃ በሻይ ብርጭቆ ተሰፍሮ ነበር የሚሰጠን፡፡ መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም ከ 1 ደቂቃ የማይበልጥ ጊዜ ነበር የሚሰጠን፡፡ ቦታውን የኦሮሚያ ልዩ ኃይልም በጊዜያዊ ካምፕነት ይጠቀምበት ስለነበረ በግቢው ውስጥ ብዙ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊሶች ነበሩ፡፡ አንድ ቀን ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ገደማ መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም በተሰለፍኩበት አንድ ፖሊስ “አትሮጥም?” በማለት ሲጠይቀኝ በደንብ መሮጥ እንደማልችል በመናገሬ ብቻ “እንዴት አትሮጥም” ብሎ በዱላ እግሬንና ጀርባዬን መታኝ። ከዛም ሰባት የሚሆኑ ሌሎች ፖሊሶች በእርግጫና በዱላ ስለደበደቡኝ ጭንቅላቴ ተፈንክቶ ደም ፈሰሰኝ፡፡ በእንብርክክ እንድሄድ እና ፑሽ አፕ እንድሰራ ሲያዙኝ ስለተጎዳሁ ፑሽ አፕ ልሰራ እንደማልችል ባስረዳም አንዱ ፖሊስ መሳሪያ አቀባበለና “እገድልሃለሁ” ብሎ አስፈራራኝ። “በቃ ግደሉኝ” ብዬ ስጮህ ሌሎች ሰዎችና የፖሊሶቹ አለቃ ስለሰማ ይህንን የፈጸሙትን ፖሊሶች ተቆጣቸው፡፡ የፖሊሶቹ አለቃ እንደምታከም ነግሮኝ ነበር፡፡ የመጀመሪያ እርዳታ በፖሊሶች ማሰልጠኛ ውስጥ በጤና ረዳት ተሰጠኝ፡፡ የደረሰብኝ ጉዳት ከባድ በመሆኑ የጤና ረዳቱ ወጥቼ ሌላ የተሻለ ቦታ እንድታከም ያዘዘ ቢሆንም የደበደቡኝ ፖሊሶች ‹‹ከዚህ ወጥቶ መታከም የለበትም፤ እዚሁ ነው መታከም ያለበት” በማለታቸው የጤና ረዳቱ ከአዳማ መድኃኒትና መሳሪያዎችን ይዞ መጥቶ ጭንቅላቴን ሰፋኝ፡፡ በዚሁ ምክንያት ለሌላ በሽታም ተጋልጫለሁ” በማለት አስረድቷል፡፡ የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድንም በእስረኛው እግር እና ጭንቅላት ላይ ጠባሳ መኖሩን እና ሌሎች የሕክምና ሰነዶችን ተመልክቷል፡፡

የመንግሥት አካላት ምላሽ 
የቡራዩ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ሲሰጡ በጣቢያው የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሲመጡ የረሃብ አድማ ላይ የነበሩ መሆኑን ገልጸው፣ ምግብ እንዲበሉ ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ማግባባታቸውን ገልጿል፡፡ ሕመም በሚያጋጥማቸው ጊዜ ደግሞ በራሳቸው በእስረኞቹ ወጪ ወደ ሕክምና ተቋም እየወሰዱ እንዲታከሙ መደረጉን ተናግረዋል። “ጉዳዩን የያዘው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በመሆኑ እኛ ይዘን ከማቆየት ውጪ የተጠረጠሩበት ጉዳይ እኛን አይመለከትም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

የኢሰመኮ የምርመራ ቡድን የገላን እና የሰበታ ፖሊስ መምሪያዎችን የጎበኘ ቢሆንም፣ ክትትሉ በተደረገበት ጊዜ በፖሊስ መምሪያዎቹ የኦነግ አመራር የሆኑ እስረኞች የሌሉ መሆኑን ከፖሊስ ተገልጾለታል፡፡ ሆኖም በሰበታ ፖሊስ መምሪያ የኦነግ ፓርቲ አባላት መሆናቸውን የገለጹ እስረኞችና እና ሁለት የኦ.ኤን.ኤን ጋዜጠኞች የነበሩ ሲሆን፣ የፖሊስ መምሪያዎቹ አመራሮች እነዚህ እስረኞች ምርመራቸው ተጠናቆ መዝገቦቻቸው ለዐቃቤ ሕግ መተላለፉንና የዐቃቤ ሕግ ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ለኢሰመኮ ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በእስረኞች በተነሱ ቅሬታዎች ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ተጠይቀው “የኦነግ አመራሮች የተባሉ ተጠርጣሪዎች በሙሉ እንደተፈቱ ነው የምናውቀው” በማለት ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ በተጨማሪም “አቶ አብዲ ረጋሳ በተመለከተ በቦረና ዞን በግድያ ወንጀል ተጠርጥረው ወደ ስፍራው እንደተወሰዱ፣ እንዲሁም ኮሎኔል ገመቹ አያና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በኩል ተፈልገው በምርመራ ላይ እንደሚገኙ፣ በእስር ላይ እያሉ ለበሽታ የተጋለጡ እስረኞችን በሚመለከት እንዲታከሙ እና እንዲለዩ ይደረጋል፣ የምግብ አቅርቦት በተመለከተ በክልሉ በቀን ለአንድ የፖሊስ ጣቢያ እስረኛ በሕግ የተፈቀደው የዕለት የምግብ ወጪ 21 ብር ቢሆንም፣ አሁን ያለውን የገበያ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የፖሊስ ኮሚሽኑ ወደ 40 ብር እንዲያድግ ማድረጉንና፣ እንደ አስፈላጊነቱ እየታየ የሚጨመር ይሆናል” በማለት ገልጸዋል፡፡ 

የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ለኢሰመኮ በሰጠው ምላሽ “የተወሰኑ የኦነግ አመራሮች በ2013 ዓ.ም. ክስ ለመመስረት የሚያስችል በቂ ማስረጃ ያልተገኘባቸው በመሆኑ የምርመራ መዝገቡ ተዘግቶ ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ መተላለፉን፣ የተወሰኑት ደግሞ ክስ ተመስርቶባቸው በፍርድ ቤት ነፃ መባላቸውን በመግለጽ በአሁኑ ጊዜ በዚህ የኢሰመኮ ምርመራ ስማቸው የተጠቀሰው እስረኞች መካከል በምርመራ ላይም ሆነ በክስ ሂደት የሚገኙ እንደሌሉ አስረድቷል።

መደምደሚያ
ኢሰመኮ በቃለመጠይቅ፣ በአካላዊ ምልከታ እንዲሁም የፍርድ ቤት፣ የዐቃቤ ሕግ እና የሕክምና ሰነዶችን በማየት ባሰባሰበው እና ባገናዘበው ማስረጃ መሰረት ከዚህ በላይ ስማቸው የተጠቀሱት እስረኞች መሰረታዊ የሕግ መርሆችን፣ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎችን እና የፍርድ ቤት ወይም የዐቃቤ ሕግ ውሳኔዎችንና ትዕዛዞችን በመቃረን በሕግ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውጪ ያለ ተገቢ የፍርድ ሂደት በእስር እንዲቆዩ መደረጋቸውን፣ በተደጋጋሚ ከቦታ ቦታ እንዲዘዋወሩ መደረጋቸውን፣ የተወሰኑት እስረኞች በተፈጸመባቸው ድብደባ ምክንያት እና ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ፤ ለተለያዩ የአካል ጉዳቶች እና የጤና ችግሮች ስለመጋለጣቸው ምክንያታዊ አሳማኝ ሁኔታ መኖሩን አረጋግጧል፡፡

ምክረ ሃሳብ

  • የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን ያለ ተገቢ የፍርድ ሂደት በእስር ላይ የሚገኙ በዚህ ሪፖርት የተዘረዘሩ እስረኞችን በሙሉ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቅ፤ እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታ በተራዘመ የቅድመ-ክስ እስር ላይ የሚገኙ ማናቸውም እስረኞችን በሚመለከት ተዓማኒ ክስ ካልቀረበባቸው በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቅ፣
  • የፖሊስ እና የፀጥታ አካላት በሙሉ የፍርድ ቤቶችን እና የዐቃቤ ሕግ ትዕዛዞችንና ውሳኔዎችን እንዲያከብሩ እና እንዲያስከብሩ፣ 
  • በእስረኞች ላይ ድብደባ የፈጸሙ የኦሮሚያ መንግሥት የፀጥታ አባሎችና ኃላፊዎች ላይ ምርመራ በማድረግ ተገቢው እርምጃዎች እንዲወሰዱና የሕግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣ 
  • ተገቢ ባልሆነ አያያዝ በእስረኞች ላይ ለደረሰው ጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው ኢሰመኮ ያሳስባል፡፡