- Version
- Download 83
- File Size 458.32 KB
- File Count 1
- Create Date October 19, 2023
- Last Updated October 20, 2023
አንኳር ጉዳዮች:- የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ሁለተኛውን ዓመታዊ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ይፋ ሲያደርግ፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ በ2015 ዓ.ም. ኮሚሽኑ ባከናወናቸው የክትትልና የምርመራ ሥራዎች የለያቸውን አሳሳቢ ጉዳዮች ለማስተካከል የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ተፈጻሚ እንዲሆኑ እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ውሳኔዎችን ከመስጠታቸው በፊት እንዲሁም ፕሮግራሞችና አገልግሎቶች በሚቀርጹበት ወቅት እንደመረጃ ምንጭ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ በማሰብ ነው። የኮሚሽኑ የመጀመሪያው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ዓመታዊ ሪፖርት ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ እንደተደረገ የሚታወስ ሲሆን፤ የሀገር ውስጥ መፈናቀል ይህ ሪፖርት በሸፈነው ከሰኔ 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2015 ዓ.ም. ወቅትም አሳሳቢ ችግር ሆኖ ቀጥሏል። የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (International Organization for Migration) እ.ኤ.አ ከኅዳር ወር 2022 እስከ ጥር ወር 2023 የሰበሰበውን መረጃ መሠረት አድርጎ በሚያዚያ ወር 2023 ያወጣው ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ3.14 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እልባት ያላገኙ፣ በተለያየ ጊዜ በሚያገረሹ ወይም በአዲስ መልኩ በሚከሰቱ የታጠቁ ቡድኖች ጥቃቶች እና ዘላቂ ፖለቲካዊ እና መዋቅራዊ መፍትሔ ባልተሰጣቸው የትጥቅ ግጭቶች ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከቀያቸው ይፈናቀላሉ። ከዚህም በተጨማሪ እንደ ጎርፍ እና ድርቅ ያሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች፣ በልማት ፕሮጀክቶች እና ሌሎች ምክንያቶች ሰዎች ለመፈናቀል ይዳረጋሉ። መንግሥት ለመፈናቀል ችግር ዘላቂ መፍትሔዎችን የማፈላለግ ኃላፊነት የተጣለበት ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ ከ1 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች በተራዘመ የመፈናቀል ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
ይህ ሁለተኛው የዘርፍ ሪፖርት በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች አያያዝና ጥበቃ ላይ ብቻ የሚያተኩር ሲሆን፤ ከሰኔ ወር 2014 እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ባሉት 12 ወራት ኮሚሽኑ ባከናወናቸው የክትትል፣ የምርመራ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የውትወታ ሥራዎች በመመርኮዝ በ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት የታዩ መልካም ጅማሮዎችን እና እመርታዎችን ለይቶል። መሠረታዊ ከሆኑት ከመንቀሳቀስ መብት እንዲሁም ከሰላም እና ደኅንነት ሁኔታ አንጻር በመገምገም ትርጉም ያለው መሻሻል እንዳይኖር ያደረጉ እና መልካም ጅማሮዎችን ወደ ኋላ የሚጎትቱ እንዲሁም በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መፍትሔ ሊያገኙ እና ሊሻሻሉ የሚገቡ አሳሳቢ ጉዳዮችን በዝርዝር አካቷል፡፡
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት