Download
Download is available until [expire_date]
  • Version
  • Download 33
  • File Size 501.91 KB
  • File Count 1
  • Create Date September 6, 2023
  • Last Updated December 6, 2023

አንኳር ጉዳዮች:- የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው የሰብአዊ መብቶች ዘርፎች መካከል የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች አንዱ ነው። ለዚህም ዘርፉን የተመለከተና በኮሚሽነር የሚመራ የሥራ ክፍል በማቋቋም፤ በአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች መብቶች ዙሪያ የግንዛቤ ማስፋፊያ፣ የሕግ ማእቀፎች አተገባበር ክትትልና ምርመራ እንዲሁም ዘርፈ-ብዙ የውትወታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ኮሚሽኑ በሕግ በተሰጡት ሥልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነቶች መሠረት ያከናወናቸውን የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራዎች፣ የዳሰሳ ጥናቶች እና የውትወታ ሥራዎች መነሻ በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀውን ይህን የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ሐምሌ 05 ቀን 2015 ዓ.ም. ካወጣው ዓመታዊ ጥቅል ሪፖርቱ ጎን ለጎን ይፋ አድርጓል።

ይህ ዓመታዊ ሪፖርት በ2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ከአካል ጉዳተኞች እና ከአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መስፋፋት አኳያ በሕግና ፖሊሲ ማዕቀፎች ላይ የተለዩ ክፍተቶች፣ የፍትሕ ተደራሽነት ሁኔታ፣ የአካል ጉዳተኞች በከፍተኛ ትምህርት የመካተት መብት ሁኔታ እና የአረጋውያን እንክብካቤ የማግኘት መብትን ጨምሮ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ዙሪያ ያለውን የማኅበረሰብ የግንዛቤ ሁኔታ አካቷል። በተጨማሪም ሪፖርቱ በ2015 ዓ.ም. የተገኙ መልካም እመርታዎች፣ መንግሥት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች፣ ማጠቃለያ እና ዝርዝር ምክረ ሐሳቦችን ይዟል።

ሪፖርቱ በዋናነት የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍልን ጨምሮ ሌሎችም የኮሚሽኑ ሥራ ክፍሎች በዓመቱ (ከሰኔ 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2015 ዓ.ም.) ባከናወኗቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራዎች፣ በግለሰቦች እና በሲቪክ ማኅበራት የቀረቡ አቤቱታዎች፣ መለስተኛ ጥናቶች እና በልዩ ልዩ የምክክር መድረኮች ላይ የተገኙ መረጃዎች እና ማስረጃዎችን አግባብነት ካላቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችና መስፈርቶች እንዲሁም ብሔራዊ ሕጎችና የፖሊሲ ማዕቀፎች አንጻር በመተንተን የተዘጋጀ ነው።

የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት

Executive Summary: Annual Human Rights Situation Report on Disability Rights and Rights of Older Persons