- Version
- Download 23
- File Size 2.68 MB
- File Count 1
- Create Date April 23, 2024
- Last Updated May 10, 2024
የ2015 በጀት ዓመት የሕግ ታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ዓመታዊ የክትትል ሪፖርት
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በፌዴራል ሕገ መንግሥት መሠረት ነጻ ፌዴራላዊ የመንግሥት አካል ሆኖ በአዋጅ ቁጥር 210/1992 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) የተቋቋመ እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነ ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት፣ መከበር እና ጥበቃ የሚሠራ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ነው፡፡
ኮሚሽኑ በማቋቋሚያ ዓዋጁ መሠረት የተለያዩ ሥልጣን እና ኃላፊነቶች የተሰጡት ሲሆን ከነዚህም መካከል በአዋጁ አንቀጽ 6(1) የተጠቀሰው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት የተደነገጉ ሰብአዊ መብቶች በማንኛውም ዜጋ፣ በመንግሥት አካላት፣ በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሌሎች ማኅበራት እንዲሁም በባለሥልጣኖቻቸው መከበራቸውን ማረጋገጥ ይገኝበታል፡፡
ይህንን ለማሳካት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ማድረግ ሲሆን ይህም ሥልጣን የሚመነጨው ከዚሁ የአዋጁ ድንጋጌ እና ከተቋሙ ዓላማ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ከታወቁት ሰብአዊ መብቶች በተጨማሪም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(4) እንደሚያስቀምጠው ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ የሕግ አካል በመሆናቸው እና በአንቀጽ 13 (2) መሠረት በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ የሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች፣ ሰነዶች እና መርሖች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ መተርጎም እንዳለባቸው በሚደነግጉት አንቀጾች መሠረት የኮሚሽኑ የክትትል ሥራዎች ከዓለም አቀፍ እንዲሁም አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች፣ መርሖች እና ሕጎች አንጻርም የሚከናወኑ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማትን ሥልጣን እና ተግባራትን የሚዘረዝረው በተባበሩት መንግሥታት የጸደቀው መርሖች (የፓሪስ መርሖች) የሰብአዊ መብቶች መከበራቸውን ማረጋገጥ በብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ከሚከናወኑ ቁልፍ ተግባራት አንዱ መሆኑ ተገልጿል።
ኮሚሽኑ በማቋቋሚያ አዋጁ በተሰጠው ሰፊ ሥልጣን እና ኃላፊነት መሠረት በሁሉም ሰብአዊ መብቶች ላይ ክትትል በማድረግ ምክረ ሐሳቦችን የማቅረብ ኃላፊነት አለበት፡፡ ለኮሚሽኑ በማቋቋሚያ አዋጁ አንቀጽ 6(13) መሠረት ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል አንዱ በሀገሪቱ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶችን ያለምንም ቅደመ ማስታወቂያ የታራሚዎችን አያያዝና ሰብአዊ መብቶች አከባበር ክትትል ማድረግ ይገኝበታል። በዚሁ መሠረት ኮሚሽኑ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሰነዶች እና ዓለም ዓቀፍ ዝቅተኛ መስፈርቶችን መሠረት በማድረግ በ2015 በጀት ዓመት በሀገሪቱ በተመረጡት ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የተከሳሾች እና ታራሚዎች የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ዙሪያ የሚስተዋሉ መልካም ተሞክሮዎች እና ተግዳሮቶችን በመለየት እና ለተስተዋሉት ተግዳሮቶች ምክረ ሐሳብ በዚህ ሰነድ ተቀናጅቶ ቀርቧል፡፡