ይህ የሩብ ዓመት ሪፖርት በኢትዮጵያ የበጀት ዓመት አቆጣጠር መሠረት ከሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. እስከ መስከረም ወር 2017 ዓ.ም. መጀመሪያ ያለውን ጊዜ የሚመለከት ቢሆንም የተወሰኑት ሁኔታዎች ቀደም ባሉት ወራት የተከሰቱና የቀጣይነት ባሕርይ ያላቸው ናቸው። በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ሥጋቶች እና አሳሳቢ ሁኔታዎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ይህ የሩብ ዓመት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በተለይ በግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ በዋነኝነት ከፍተኛ በሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና አሳሳቢነታቸው በቀጠሉ ጉዳዮች ላይ ማሳያ በሆኑ ክስተቶች አጠቃላይ ምልከታ በመስጠት ለሰብአዊ መብቶች ሁኔታ መሻሻል ምክረ ሐሳቦችን የሚያቀርብ ነው።