የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሀገር ውስጥ በሴቶች እና በሕፃናት የመነገድ ድርጊትን ለመግታት በሚወሰዱ ምላሾች ላይ ባከናወነው ክትትል የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አተገባበርን አስመልክቶ ሰኔ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል። በመድረኩ ከፌዴራልና ከክልል ተቋማት የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ከአዲስ አበባ፣ ከአዳማ፣ ከባሕር ዳር፣ ከሐዋሳ እና ከወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከምሥራቅ ሸዋ ዞን የተወጣጡ የፍትሕ ተቋማት፣ አስፈጻሚ አካላት፣ የሥራ ኃላፊዎች እና ተወካዮች ተገኝተዋል።

በውይይቱ በሴቶች እና በሕፃናት የመነገድ ድርጊትን ለመግታት የተካሄዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ጥናትና ምርምር፣ የሥራ እቅዶችና መመሪያዎች አተገባበር፣ የአቤቱታና የጥቆማ ሥርዓት፣ የወንጀል ምርመራ፣ የክስ አቀራረብና ተጠያቂነት እንዲሁም የተጎጂዎች የደኅንነት ጥበቃና መልሶ ማቋቋም የቅንጅት ሥራዎችን በተመለከተ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አተገባበር እና ሌሎች በክትትሉ የተለዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መከናወናቸው፣ መደበኛ ባልሆኑ የሥራ ዘርፎች ላይ ክትትል የሚደረግ መሆኑ፣ የጥቆማ ሥርዓትን መዘርጋት መቻሉ እንዲሁም ከዐቅም ማሳደጊያ እና መልሶ ማቋቋም አንጻር የተወሰዱ እርምጃዎች በውይይቱ በአዎንታዊነት ተነስተዋል። በሌላ በኩል ከተደራጀ መረጃ አያያዝ፣ ከወንጀል ምርመራ እና ክስ አመሠራረት፣ እንዲሁም ከጥናት እና ምርምር ተግባራት አንጻር አሁንም ክፍተቶች መኖራቸው በአሳሳቢነት ተመላክቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች መልካም ጅምሮችን ማስቀጠልና በአሳሳቢነት የቀጠሉ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በማኅበረሰብ አመለካከት ለውጥ ላይ በስፋት መሥራት፣ የሕግ ክፍተቶችን ማስተካከል፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማሳደግና የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል። በተጨማሪም ለፍትሕ አካላት ስልጠና መስጠት እንዲሁም በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው የተጎጂዎች ፈንድና የፍልሰት ፖሊሲ ጸድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር አሸነፈች አበበ በሀገር ውሰጥ በሴቶች እና ሕፃናት የመነገድ ድርጊትን ለመግታት የተወሰዱ እርምጃዎች፣ የወጡ ሕጎችና የተቋቋሙ የማስተባባሪያ ማእከላት አበረታች ጅምሮች መሆናቸውን ገልጸው፤ ከችግሩ ስፋት አንጻር ሕጎችን በቁርጠኝነት መተግበር፣ ክፍተቶችን መሙላትና የባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ አሠራር ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል። አክለውም የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።