የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች ምላሽ አሰጣጥን በተመለከተ በተለይም የሕግ፣ የአተገባበር እና የአሠራር ክፍቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገ እና የዳኞችን ግንዛቤ ለማጎልበት ያለመ የውይይት መድረክ ታኅሣሥ 24 እና 25 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል። በውይይቱ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቤተሰብ ምድብ ችሎት፣ የተጠቂ ሴቶች እና ሕፃናት ምድብ ችሎት እና ወንጀል ውስጥ የገቡ ሕፃናት ምድብ ችሎት ዳኞች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የማኅበራዊ ሳይንስ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር፣ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ዳኞች ፎረም ሰብሳቢ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሻል ወርክና የሕግ ትምህርት ቤት ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኀበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የኢሰመኮ ተወካዮች የውይይት መነሻ ሐሳብ አቅርበዋል።

በመድረኩ በሴቶችና ሕፃናትና ላይ የሚደርሱ የቤት ውስጥ ጥቃቶችና አሉታዊ ተጽዕኖዎች፣ የማገገሚያ መንገዶች፣ ጥቃቶቹ በፍርድ ቤት የሚስተናገዱበት አግባብ፣ በፍርድ ቤቶች ውስጥ የማኀበራዊ ሳይንስ አገልግሎት አሰጣጥና አሠራር ላይ ያሉ ክፍተቶች እና በጎ ተሞክሮዎች፣ በጋብቻ እና ኢኮኖሚያዊ ውጤቶች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተነስተዋል። ኢሰመኮ ያካሄደው በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የጥቃት ተጎጂ ሴቶች እና ሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አያያዝን የተመለከተ ክትትል ሪፖርት ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች በተመሳሳይ ቀርበዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በሴቶችና ሕፃናት ችሎት የሚሠሩ ዳኞች ያለባቸውን የሥራ ጫና መቋቋሚያ፣ መከላከያ መንገዶች እና በስብዕና ላይ የተመሠረተ አመራር ክሕሎት በተለይም በሴቶችና ሕፃናት መብቶች አጠባበቅ ዙሪያ ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ የቤት ውስጥ ጥቃቶች በፍርድ ቤት በሚሰጥ ዳኝነት በሚገኝ ፍትሕ ብቻ የሚያበቁ ባለመሆናቸው የሕክምና፣ የሥነ ልቦና እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ በዘላቂነት ማግኘት የሚችሉበት የቅብብሎሽ ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ ገልጸዋል። በሌላ በኩል ለቤት ውስጥ ጥቃቶች ተጎጂዎች የተፋጠነ ፍትሕ ለመስጠት የሚረዳ የፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ ወጥና ራሱን የቻለ የመረጃ መቀበያ ሥርዓት መዘርጋትን ጨምሮ ጉዳዮችን በልዩ ችሎት ማስተናገድ እንዲሁም ሕጎችን ማስፈጸሚያ ደንቦች እና መመሪያዎችን ማውጣት እንደሚገባ ተጠቁሟል።

በተመሳሳይ በሴቶችና ሕፃናት አንዲሁም በቤተሰብ ችሎት የሚመደቡ ዳኞች ስልጠና ያገኙ እና በቂ ልምድ ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ፣ ተጎጂዎች ወደ ችሎት ከመግባታቸው በፊት የንቃተ ሕግ ትምህርት ሊያገኙ የሚችሉበትን እና ምስክር ሆነው ችሎት በሚቀርቡበት ወቅት የሚጋጥማቸውን ፍርሀት ለመቀነስ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር እና የማስመስከር ሂደቱን ቀልጣፋ ማድረግ እንደሚገባ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አሸነፈች አበበ ፍርድ ቤቶች የሰብአዊ መብቶችን በማስጠበቅ ረገድ ወሳኝ ሚና ያላቸው እንደመሆኑ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ የቤት ውስጥ ጥቃቶች ተጎጂዎች የተቀላጠፈ እና ፈጣን ፍትሕ እንዲያገኙ በፍርድ ቤት አስተዳደር፣ በሕግ ማሻሻያ እና ከዳኞች አንፃር ያሉ አሠራሮችን በመፈተሽ እና ክፍተቶችን በአፋጣኝ በመለየት የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል። የቤት ውስጥ ጥቃቶችን የተመለከተ የተቀናጀ የመረጃ ማእከል ማደራጀት እና በልዩ ችሎት ሊታይ ይገባል በሚል በውይይት የተነሱ ነጥቦች በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚታዩ አመላክተዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮች መሠረት በማድረግ ቀጣይ ሥራዎችን ለማሳካት ሁሉም የፍትሕ ዘርፍ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ እና በቅንጅት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም ኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች አያያዝ ሁኔታን በመከታተል እና በመመርመር በግኝቶች ላይ የተመሠረቱ ምክረ ሐሳቦችን ለባለድርሻ አካላት ማቅረብና ተፈጻሚ እንዲሆኑ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።