የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይም በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ ውስጥ እና በተወሰኑ አካባቢዎች በሸገር ከተማ በመንግሥት አካላት ከፈረሱ መስጊዶች ጉዳይ ጋር ተያይዞ የተነሱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ የደረሰውን የሰዎች ሞት እና ጉዳቶችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ከመንግሥት የጸጥታ አካላት ኃላፊዎች፣ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የሕክምና አገልግሎት ካገኙባቸው የጤና ተቋማት ኃላፊዎች፣ ዐይን እማኞች እና ከተጎጂዎች ማስረጃ በማሰባሰብ እና ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል።
ኢሰመኮ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ባሰባሰበው መረጃና ማስረጃዎች መሠረት የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎችና የአድማ ብተና ኃይል ወደ ታላቁ አንዋር መስጊድ ግቢ ጭምር በመግባትና አስለቃሽ ጋዝ በመተኮስ ምእመናንን እና የተሰበሰበውን ሰው ለመበተን እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት የ2 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ በርካቶች ላይ አካላዊ ጉዳት መድረሱን፣ በጸጥታ ኃይል አባላት ላይም ጉዳት መድረሱን እና በወቅቱ ወደ 140 የሚሆኑ ሰዎች በጥፋት ተጠርጥረዋል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ መሆኑን ኢሰመኮ ለመረዳት ችሏል፡፡
በተጨማሪም ግንቦት 18 እና 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር ውለው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ፣ በአውቶብስ ተራ እና በመርካቶ ፖሊስ ጣቢያ የተያዙ ሰዎችን በመጎብኘት ክትትል አድርጓል፤ ተጠርጣሪዎቹ በቤተሰባቸው ሲጎበኙ ተመልክቷል። ቅዳሜ ግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የተያዙት ተጠርጣሪዎች ደግሞ ሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በተመሳሳይ ችሎት ቀርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ለመርማሪ ፖሊስ 10 የምርመራ ቀናትን በመፍቀዱ ተጠርጣሪዎቹ ለግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ መሰጠቱን ኮሚሽኑ ተመልክቷል፡፡
ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ኃላፊዎች ምክር ቤቱ የእራሱን ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃላፊዎች በበኩላቸው የደረሰውን ጉዳት በማጣራት እና ጉዳት ያደረሱ የጸጥታ አካላትን ለመለየት ምርመራ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተለይም በክስተቱ የሞቱ እና አካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ጉዳይ በሚመለከት ከአዲስ አበባ እና ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽኖች የተውጣጣ የምርመራ ቡድን መቋቋሙን ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡
ኢሰመኮ እነዚህን ማስረጃዎች እና ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በመንግሥት አካላት በተወሰዱ እርምጃዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎችንም ማስረጃ ጨምሮ የሚያደርገውን ክትትል የሚቀጥል ይሆናል። ይሁንና የመንግሥት የጸጥታ አካላት በማንኛውም ዓይነት ሰላማዊ ሕዝባዊ ሰልፎች፣ ሃይማኖታዊ እና ሌሎች ስብስቦችን አላስፈላጊና ተመጣጣኝ ካልሆነ እና ሞት ከሚያስከትል የኃይል እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠቡ በድጋሚ ያሳስባል፣ ይህንን ዓይነት ኃይል መጠቀም በተመለከተም ግልጽ አመራር ሊሰጥ እንደሚገባ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ያቀረበውን ጥሪ በድጋሚ ያስታውሳል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አክለውም የመንግሥት የጸጥታ አካላት አላስፈላጊና ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል የመጠቀም አዝማሚያ እየጨመረ መምጣቱን እና በዚህም ሳቢያ በሰዎች ላይ ሞት፣ የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት እንዲሁም ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እየደረሱ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጨምሮ በተለያየ ወቅት ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማመልከቱን እና ውትወታ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። “በተለይም ሰላማዊ የሆኑ ሃይማኖታዊ ስብስቦች ወቅት የሚወሰድ እርምጃ በተለይም የመንግሥት የጸጥታ አካላትን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ መሆኑን በድጋሚ እናሳስባለን” ያሉት ዶ/ር ዳንኤል፣ ለሰው ሕይወት እልፈትና አካል ጉዳት ተጠያቂ የሆኑ የጸጥታ አካላት ተለይተው በሕግ እንዲጠየቁ፣ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ወንጀል ስለመፈጸማቸው በቂ ጥርጣሬ ከሌለ እና ተዓማኒ ክስ የማይቀርብ ከሆነ በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ወይም በሕግ አግባብ በእስር ላይ ያሉ ሰዎች የዋስትና መብት ሊከበር ይገባል ብለዋል።