የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ ለኢትዮጵያ የሰጣቸው የማጠቃለያ ምልከታዎች እና የማራኬሽ መግለጫ ላይ ከመንግሥት አስፈጸሚ አካላት ጋር ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ ኮሚቴው ለኢትዮጵያ የሰጣቸውን ምልከታዎች እና የማራኬሽ መግለጫን ይዘት ለባለድርሻ አካላት ለማስገንዘብ እና በአፈጻጸም ሁኔታ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለመ ነው።



በመድረኩ የዓለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን አፈጻጸምን በተመለከተ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረበችውን ወቅታዊ ሪፖርት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ ጥቅምት 7 እና 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ግምገማ ላይ በመመሥረት ጥቅምት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. የሰጣቸው የማጠቃለያ ምልከታዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።



በተጨማሪም በመድረኩ የሲቪክ ምህዳሩን በማስፋት፣ ለሴቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት የሰብአዊ መብቶች ተማጋቾችን በማጠናከርና በመጠበቅ ረገድ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ያላቸውን ሚና የሚገልጸው የማራኬሽ መግለጫ የአማርኛ ትርጉም ሕትመት ለተሳታፊዎች የተሰራጨ ሲሆን የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች፣ የብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ሚና፣ የሰብአዊ መብቶች ማስፋፋት፣ ጥበቃ፣ ትብብር እና አጋርነትን የተመለከቱ የመግለጫው ይዘቶች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል። በመጨረሻም ተሳታፊዎች ኮሚቴው የሰጣቸው ምከረ ሐሳቦችን ለማስፈጸም በተዘጋጀ የድርጊት መርኃ ግብር ላይ ውይይት አድርገዋል።

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል በሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ ለኢትዮጵያ የተሰጡ የማጠቃለያ ምከረ ሐሳቦችን መተግበር የሁሉም የመንግሥት ተቋማት ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።