በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የቀድሞ የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን በ2011 ዓ.ም. መፍረሱን ተከትሎ በዲራሼ ልዩ ወረዳ ከመዋቅር እና የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ፣ በተፈጠሩ ግጭቶች የሰዎች ሞት፣ መፈናቀል እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአካባቢው በተፈጠረው ግጭት ላይ ክትትል እና ምርመራ በማድረግ ከክልሉ መንግሥት ጋር በቅርበት ሲሠራ ቆይቷል። ግጭቱ የተወሳሰበ እና ዘርፈ ብዙ እንደመሆኑ መጠን አካታች (inclusive)፣ ሁሉን አቀፍ (comprehensive) እና ዘላቂ መፍትሔ ሊፈለግለት የሚገባ በመሆኑ ይህ እንዲደረግ ኢሰመኮ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ግጭቱን በዘላቂነት ለማስቆም እና በግጭቱ ምክንያት የሚፈጠሩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለማስቀረት ኢሰመኮ ግጭቱ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ያደረጋቸው የክትትል እና የምርመራ ግኝቶችን መሰረት በማድረግ የተለዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ቀርበው ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የማኅበረሰብ ተወካዮች እና ተገቢነት ያላቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሐምሌ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በሃዋሳ ከተማ የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱ ይታወሳል።
የዚሁ የምክከር መድረክ ቀጣይ የሆነው ሁለተኛ ዙር የምክክር መድረክ ኅዳር 17 እና 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሁሉም የልዩ ወረዳው ብሔረሰቦች የተወጣጡ ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የወጣቶች፣ የሴቶች እና የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች፣ የወረዳው አስተዳደር፣ የክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ፣ የክልሉ የልዩ ኃይል ፖሊስ፣ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ፍትሕ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የሰላም ሚኒስቴር በተገኙበት በአርባ ምንጭ ከተማ የሁለት ቀናት ውይይት ተደርጓል፡፡
በመጀመሪያው ቀን ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉም አካላት በተገኙበት የኢሰመኮ የክትትል እና ምርመራ ግኝቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። በሁለተኛው ቀን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተወካዮች ብቻ የተሳተፉበት በመጀመሪያው ቀን የቀረቡ የምርመራ እና ክትትል ግኝቶችን እንዲሁም ከተሳታፊዎች የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት በማድረግ በቀጣይ በአካባቢው የተፈጠረውን ግጭት በዘላቂነት ለማስቆም እና የነዋሪዎችን ሰብአዊ መብቶች ለማስከበር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ በመምከር የድርጊት መርኃ ግብር የማዘጋጀት ሥራ ተሰርቷል፡፡ የድርጊት መርኃ ግብሩ ሰላም ለማስፈን፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፣ እርቅ ለማውረድ፣ መልሶ ማቋቋም እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን የተመለከቱ በቀጣይ መሠራት ያለባቸው አራት ዋና ዋና ተግባራትን የያዘ ነው፡፡
የተዘጋጀው የድርጊት መርኃ ግብር ዝርዝር የአፈጻጸም እቅድ ተዘጋጅቶለት በክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ መሪነት እና ተገቢነት ባላቸው ሌሎች ቢሮዎች ፈጻሚነት ተግባራዊ እንዲደረግ መግባባት ላይ ተደርሷል። በተጨማሪም ከማኅበረሰብ ተወካዮች በቀረበው ጥያቄ መሰረት በዚህ መድረክ የተዘጋጀውን የድርጊት መርኃ ግብር አፈጻጸም የሚከታተል እና እንደ አስፈላጊነቱ የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርግ ሱፐርቫይዘሪ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ምርመራ እና ክትትል ሪጅናል ዳይሬክተር ኢማድ አብዱልፈታህ፣ የክልሉ መንግሥት እና ማኅበረሰቡ ችግሩን ለመፍታት ያሳዩት ተነሳሽነት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ ለእቅዱ መሳካት ሰላም የማስፈን፣ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ፣ እርቅ የማውረድ፣ መልሶ ማቋቋም እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሥራዎች በቀረበው የድርጊት መርኃ ግብር መሰረት በአንድ ማዕቀፍ ስር ተግባራዊ እንዲደረጉ አጽንኦት ሰጥተው ጠይቀዋል፡፡
ኢሰመኮ ይህ እቅድ እንዲሳካ እና በአካባቢው የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በዘላቂነት እንዲቆሙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልል እና የፌዴራል የመንግሥት አካላት ግጭቱ ያስከተለውን የማኅበራዊ እና ሰብአዊ ቀውስ በመረዳት ለጥረቱ መሳካት ድርሻቸውን በኃላፊነት እንዲወጡ እያሳሰበ፤ የተዘጋጀውን የድርጊት መርኃ ግብር አፈጻጸም በቅርበት መከታተሉንና እና መደገፉን የሚቀጥል መሆኑን ይገልጻል፡፡