የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎችና በርካታ ተመልካቾች በተሰበሰቡበት አስክሬኖች እና አንድ በሕይወት የነበረ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ እሳት ውስጥ ሲጨመር የሚያሳይና በማኅበራዊ ሚድያ በተሰራጨ የቪድዮ ምስል በደረሱት ጥቆማዎች መሰረት ስለሁኔታው አፋጣኝ ማጣራት አድርጓል። ኢሰመኮ ምስክሮችን በማነጋገር እንዳጣራው ክስተቱ የተፈጸመው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን በጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ ውስጥ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. መሆኑን፣ ከዳኝነት ውጪ የተፈጸመ ግድያ (extra-judicial killing) እና አስከሬኖችን አንድ በሕይወት ከነበረ ሰው ጭምር የማቃጠል ድርጊቱ የተፈጸመው በመንግሥት የፀጥታ አባላትና ሌሎችም ሰዎች ተሳትፎ ጭምር የነበረ መሆኑን አረጋግጧል። እንዲሁም ለዚህ ክስተት መነሻ ስለሆነው ድርጊቱ ከተፈጸመበት አንድ ቀን በፊት ቢያንስ በ 20 የመንግሥት ፀጥታ አባላት እና በሲቪል ሰዎች ላይ በታጣቂዎች ስለተፈጸመው ግድያ ሁኔታም አረጋግጧል፡፡
የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በመተከል ዞን፣ በጉባ ወረዳ፣ አይሲድ ቀበሌ፣ አፍሪካ እርሻ ልማት ማኅበር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ገደማ፣ ከግልገል በለስ ከተማ በመኪና ተሳፍረው፣ በአካባቢው ካለው የደኅንነት ስጋት አንጻር በተለመደው አሰራር መሰረት በመከላከያ ሠራዊት ታጅበው ወደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ፤ ወደ ማንኩሽና ወደ አሶሳ ከተማ ሲጓዙ የነበሩ ሰዎች ላይ ታጣቂዎች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ፈጸሙ። በጥቃቱም 1 መኪና አሽከርካሪ፣ 1 በንግድ ሥራ የሚተዳደሩ ሰው እና 1 መምህር በአጠቃላይ 3 ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል፤ መንገደኞቹን አጅቦ በመጓዝ ላይ የነበሩት የመከላከያ ሠራዊት አባላት መኪና በከባድ መሳሪያ ተመትቶ ሻለቃ አመራሩን ጨምሮ ቢያንስ 20 የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሞተዋል፣ እንዲሁም 14 የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡
በዕለቱ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና እና ጥቃቱን በፈጸሙ የታጠቁ ኃይሎች መካከል የተደረገው ውጊያ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ ረፋዱ 12፡00 ሰዓት የቆየ ሲሆን፣ በማግስቱ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ተጨማሪ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በቦታው ደርሰው ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ 4፡00 ሰዓት ድረስ በቆየ የተኩስ ልውውጥ ከታጣቂዎቹ መካከል ወደ 30 የሚሆኑ መገደላቸውንና ቀሪዎቹ ታጣቂዎች መሸሻቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡
ይህንን ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት የመንግሥት ፀጥታ አባላቱና የሲቪል ሰዎች መንገደኞች መኪኖች የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀኑ 6፡00 ሰዓት አካባቢ አይሲድ ከተማ ደረሱ። በተከሰተው አደጋም የከተማው ፀጥታ ሁኔታ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ።
የመንግሥት የፀጥታ አባላቱ አግኝተናል ባሉት ጥቆማዎች መሰረት በአካባቢው በነበሩ ተሽከርካሪዎችና በመኖሪያ ቤቶች ላይ እንዲሁም ከግልገል በለስ ከተማ ወደ ማንኩሽና ባምዛ የሚጓዙ የነበሩ ሲቪል ሰዎች ላይ ፍተሻ ማካሄድ ጀመሩ።
በፍተሻው ሂደት ውስጥ በቅርቡ ከእስር ተፈትተው ከመተከል ዞን ማረሚያ ቤት የይለፍ ወረቀት በመያዝ ወደ መኖሪያቸው የተመለሱና የአካባቢው ነዋሪዎች የነበሩ 8 የትግራይ ተወላጆችን “እናንተ ናችሁ መረጃ ሰጥታችሁ ጥቃቱን ያስፈጸማችሁት” በማለት ከተሳፈሩበት መኪና እንዳስወረዱና በፍተሻውም አንድ የወታደራዊ መገናኛ ሬዲዮ፣ የተለያዩ ፎቶግራፎች እና ከ40,000 ብር በላይ ገንዘብ እንደተገኘ ተገልጿል። የመንግሥት ፀጥታ አባላቱም ተጠርጣሪዎቹን እየደበደቡ ተጨማሪ መረጃ መጠየቅ ጀመሩ።
ከዚህ ተከትሎም ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ “በአካባቢው በተፈጸመው ጥቃት ላይ እጃችን አለበት፤ ባምዛ በሚባለውና በግልገል በለስ ቦታዎች ሰዎች አሉን” ማለቱን ተከትሎ፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላቱ ሁኔታውን የተቃወሙ ሁለት የጉሙዝ ተወላጆችን ጨምሮ 10 ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል።
ከዚህ በመቀጠልም የፀጥታ ኃይል አባላቱ የተገደሉትን ሰዎች አስከሬኖች ከከተማዋ ወጣ ብሎ ወደሚገኝ ጫካ ስፍራ በመውሰድ አስክሬናቸውን ማቃጠል መጀመራቸውን የዓይን ምስክሮች አስረድተዋል። በዚህ መካከልም ከተጠርጣሪዎቹ ተገዳዮች ጋር ግንኙነት አለው የተባለን አንድ ሌላ የትግራይ ተወላጅ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተሳፈረበት መኪና ውስጥ ተደብቆ በጥቆማ ካገኙት በኋላ በገመድ አስረው በመውሰድ ቀድሞ በመቃጠል ላይ ከነበሩት አስክሬኖች ላይ እንደጨመሩት እና በእሳት ተቃጥሎ እንደሞተ ምስክሮች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡
በአካባቢው የነበሩት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የአማራ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላትና የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት ሲሆኑ፤ በአጠቃላይ ሁኔታው በቀጥታ ድርጊት በመፈጸም ወይም አስገዳጅ ተግባሮችን ባለመፈጸም (by commission or omission) የነበራቸው የተለያየ የተሳትፎ መጠን በተጨማሪ የወንጀል ምርመራ ሊጣራ የሚገባው ነው፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንደገለጹት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እጅግ ፈታኝ በሆኑ አካባቢዎች በከፍተኛ መስዋዕትነት የሕዝብ ደኅንነት የሚጠብቁ መሆኑ የማይዘነጋ ሕዝባዊ አገልግሎት መሆኑ እንደሚታወቅ ገልጸው፤ ሆኖም ግን በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ከዳኝነት ሂደት ውጭ መግደል እና በተለይም በእሳት አቃጥሎ መግደል ፈጽሞ ከሕግ አስከባሪ አባሎች የማይጠበቅ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በመሆኑ የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በተጠርጣሪዎች ላይ ተገቢውን የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ እንዲደረግ አሳስበዋል። ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አክለውም “የመንግሥት ሕግ አስከባሪ አባሎች እራሳቸው በግልጽ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጻሚዎች ሆነው መታየታቸው፤ ሰዎች በሕጋዊ ሥርዓት ላይ የሚኖራቸውን እምነት የሚሸረሽርና ለተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚያጋልጥ በመሆኑ፤ መንግሥት የምርመራውን ሂደትና ውጤት በተመለከተ የተሟላ መረጃ ለሕዝብ ይፋ ሊያደርግና ፍትሕን ለማረጋገጥም የሟች ቤተሰቦችን ሊክስ ይገባል” ብለዋል።