የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት (AAU-SoL) እና ከኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት ቤቶች ማኅበር (ELSA) ጋር በመተባበር፤ ‘’ምርምርና ፖሊሲን ማቀናጀት ለዘላቂ ሰላም’’ በሚል ርዕስ ዓለም አቀፍ የሽግግር ፍትሕ የምርምር ጉባኤ ከመጋቢት 18 እስከ 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል። ጉባኤው የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት በሚገኝበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በምርምር፣ በፖሊሲ እና በአፈጻጸም መካከል ያለውን ቅንጅት ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡
በጉባኤው የፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የሕግ ምሁራን እና ባለሙያዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሳትፈዋል።



በጉባኤው የወንጀል ተጠያቂነት ማስፈን፣ እውነትን መፈለግ፣ የማካካሻ ሥርዓት፣ ተቋማዊ ማሻሻያ፣ ተሳትፎና አካታችነት እንዲሁም የባለድርሻ አካላትን ሚና የሚቃኙ ትይዩ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። በእነዚህ መድረኮች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ከአህጉራዊ እና ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች አንጻር ዳሰሳ ቀርቦበታል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ለሚዘጋጀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ሕግ ተከታታይ መጽሔት (AAU-SoL Ethiopian Human Rights Law Series) ልዩ ዕትም የተዘጋጁ 20 ረቂቅ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ሙያዊ የአቻ ግምገማ (Peer review) ተደርጎባቸዋል። ይህም የጥናቶቹን ጥራት ከማጎልበት ባለፈ፣ ለፖሊሲ ቀረጻ የሚረዱ ጠቃሚ ግብዓቶች እንዲገኙ አስችሏል።



በውይይት መድረኮቹ የሽግግር ፍትሕ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ያለው ሚና እንዲሁም ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት እና የአፍሪካ ኅብረት ለተዓማኒ፣ ተጨባጭ እና ውጤታማ የሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚያደርጉት ድጋፍ አጽንዖት ተሰጥቶታል። በተጨማሪም በቀጣይ የአፈጻጸም ሂደቶች ተቋማዊ ቅንጅትን ማጠናከር እና ካለፉ ተሞክሮዎች መማር አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል።





የጉባኤው ተሳታፊዎች ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በቅንጅት መሥራትና ተቋማዊ ዝግጁነት እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ጠንካራ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ዲን ፕሮፌሰር ሙራዱ አብዶ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ሂደትን ለመደገፍ ቀጣይነት ያለው የአካዳሚክ እና የፖሊሲ ትብብር እንዲሁም ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የመውሰድ አስፈላጊነትን ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል፤ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው መጽደቅ ትልቅ እመርታ መሆኑን አንስተው፣ በቀጣይ ዋናው ትኩረት ሊሆን የሚገባው ውጤታማ አፈጻጸም፣ ተቋማዊ ግንባታ፣ የሕዝብ አመኔታን ማግኘትና የተጎጂዎችን ፍላጎት ማሳካት መሆኑን አስገንዝበዋል። አክለውም የፖሊሲና የተግባር ክፍተቶችን ለመሙላት ጥልቅ ምርምርና አካታች ውይይት አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ፤ ኢሰመኮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰብአዊ መብቶችን የሚያከብርና ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ የሽግግር ፍትሕ እንዲተገበር ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።