የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከዴንማርክ የሰብአዊ መብቶች ኢንስቲትዩት (DIHR) በተገኘ ድጋፍ፣ ከነሐሴ 25 እስከ ነሐሴ 26 ቀን 2018ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እና ሰብዓዊ መብቶች ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት የአቅም ግንባታ እና የምክክር አውደ ጥናት አካሂዷል። በአውደ ጥናቱ የመንግሥት ተቋማት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የትምህርትና ምርምር ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ታድመዋል።

አውደ ጥናቱ ባለድርሻ አካላት ስለ አየር ንብረት ለውጥ የሰብአዊ መብት ገፅታዎች ያላቸውን ግንዛቤ ለማጠናከር፣ የኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ የህግና የፖሊሲ ማዕቀፎች ከሰብዓዊ መብቶች መርሆዎች አንጻር የሚገመግመውን የኢሰመኮ ጥናት ግኝቶች ለማረጋገጥ ያለም መድረክ ሲሆን፣ የአየር ንብረት ለውጥ በሰብአዊ መብቶች ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ ለመወያየት እና በኢትዮጵያ በሰብአዊ መብት ላይ የተመሰረቱ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሾችን ለማጠናከር የሚያስችሉ መንገዶችን ለመቃኘት ያለመ ነበር።

በአውደ ጥናቱ ወቅት ከኢሰመኮ፣ ከዴንማርክ የሰብዓዊ መብቶች ኢንስቲትዩት ፣ ከኢትዮጵያ ሚትዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ከኢኮ-ጀስቲስ ኢትዮጵያ፣ ከአፍሪካ ብሔራዊ ሰብአዊ መብት ተቋማት ጥምረት (NANHRI) እና ከቁም ለአካባቢ የተውጣጡ ባለሙያዎች ገለጻዎችን አቅርበዋል፤ መድረኩ ተሳታፊዎቹ ሰብአዊ መብትን መሰረት ያደረገ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለማጎልበት ልምድና ተሞክሮ እንዲለዋወጡ አስችሏል። አውደ ጥናቱ የአየር ንብረት አስተዳደርና የመንግሥት ግዴታዎችን፣ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን፣ በአየር ንብረት ለውጥና ሰብአዊ መብቶች መካከል ያለውን ግንኙነት፣ ሰብአዊ መብትን መሰረት ያደረገ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽን ፣ ተጠያቂነትና ከአየር ንብረት ጋር ለተያያዙ ጉዳቶች መፍትሄዎችን፣ የአካባቢ ጥበቃ የህዝብ ጥቅም ክርክሮችን፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሁነቶች አማካኝነት ሰብአዊ መብትንና የአየር ንብረት ፍትህን ለማራመድ ያሉ እድሎችን ጨምሮ ቁልፍ ጉዳዮችን ዳስሷል።

ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ያልተስተካከለ የዝናብ ሁኔታ፣ የመሬት ናዳ እና ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ በሽታዎች ኑሮን በቀጥታ አደጋ ላይ እየጣሉ ናቸው። እየተባባሱ ያሉት እነዚህ የአካባቢ ቀውሶች ለህይወት፣ ለምግብ፣ ለውሃ፣ ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለዘላቂ ኑሮ እና እንደ በቂ መጠለያ ካሉ መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች አጠቃቀም ጋር የተያያዙ መብቶችን እያዳከሙ ሲሆን፣ በአየር ንብረት ምክንያት የሚደርስ የመፈናቀል አደጋንም እያባባሱ ነው።

የአውደ ጥናቱ ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ ስለ አየር ንብረት ለውጥና ሰብአዊ መብቶች የተዘጋጀውን የኢሰመኮ ግምገማ ማቅረብና ማረጋገጥ ነበር። ተሳታፊዎች በግምገማው ግኝቶችና ምክረ ሃሳቦች ላይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ ሰብአዊ መብትን መሰረት ያደረገ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽን ለማጠናከር ስለሚወሰዱ እርምጃዎችም ተወያይተዋል። እንዲሁም ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ የሰብአዊ መብት ተግዳሮቶችን ለመፍታት እና የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽን አካታችነት ለማረጋገጥ በመንግሥት ተቋማት፣ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ በትምህርት ተቋማት፣ በልማት አጋሮች እና በተጎዱ ማህበረሰቦች መካከል ቀጣይነት ያለው ትብብር የሚኖረው ጠቀሜታ ላይ አጽንኦት ተሰጥቶበታል። የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን በአየር ንብረት ህጎች፣ ፖሊሲዎች፣ የማላመድ እርምጃዎች እና በአየር ንብረት ፋይናንስ ውስጥ በተሻለ መልኩ ማካተት እንደሚያስፈልግ ተነስቷል።

በአውደ ጥናቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ፣ የአየር ንብረት ለውጥ በሰዎች ህይወት፣ ኑሮ እና መሰረታዊ መብቶች ላይ በሚያደርሰው ቀጥተኛ ተጽዕኖ የተነሳ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። የፖሊሲ አውጪዎችና ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ሁሉንም ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሾች በሰብዓዊ መብት መርሆች ላይ መመስረት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ወደፊት፣ ኢሰመኮ ግምገማውን አጠናቅቆ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰብአዊ መብትን ማዕከል ያደረገ የአየር ንብረት አስተዳደርን ለማስፋፋት ባለድርሻ አካላትን ማሳተፉን ይቀጥላል። ኢሰመኮ የህዝብ ግንዛቤን ለማሳደግ፣ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ የሰብአዊ መብት ተጽዕኖዎችን ለመከታተል እና በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ ማህበረሰቦች ጥበቃ ለመሟገት የሚያደርገውን ጥረት የበለጠ ያጠናክራል፣ ይህም በኢትዮጵያ በሰብአዊ መብት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እንዲሻሻል አስተዋፅኦ ያደርጋል።