የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የ2015 ዓ.ም. የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርትን መነሻ በማድረግ ባለመብቶች እና ባለግዴታዎች ሊኖራቸው በሚገባው ሚና ዙሪያ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. አካሂዷል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የፌዴራል እና የተለያዩ የክልል ከተሞች የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ማኅበራት፣ የመንግሥት ተቋማት እና የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
ኮሚሽኑ የ2015 ዓ.ም. የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ለተሳታፊዎች ያቀረበ ሲሆን በዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የታዩ ቁልፍ እመርታዎች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ አሳሳቢ ሁኔታዎች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል። በተጨማሪም በአረጋውያን እና በአካል ጉዳተኞች መብቶች ላይ ያተኮሩ ሁለት የፓናል ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን በውይይቶቹ ኮሚሽኑን ጨምሮ በአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ዙሪያ የሚሠሩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በፓናሊስትነት ተሳትፈዋል።
በውይይቱ በአረጋውያን ላይ የሚደርሱ ዘርፈ ብዙ የመብቶች ጥሰቶች አረጋውያን በማኅበረሰቡ ውስጥ በእኩልነት እና በክብር እንዳይኖሩ የሚያደርግ መሆኑ፣ በሀገራችን ሁሉን አቀፍ የጡረታ ሥርዓት አለመኖር እና አረጋውያን በወጣትነት ዕድሜያቸው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ለሀገር ያበረከቱትን ውለታ ከግምት ያላስገባ መሆኑ ተመላክቷል። በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የአረጋውያን መብቶች ስምምነት አለመኖር በአረጋውያን ላይ ለሚደርሱ የመብት ጥሰቶች ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያደናቅፍ በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም አካላት ይህ ስምምነት እንዲኖር የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ እንደሚገባ በውይይቱ ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ በተካሄደው የፓናል ውይይት ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ያጸደቀች ቢሆንም አተገባበሩ ላይ ከፍተኛ ክፍተት በመኖሩ አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዳይችሉ ማነቆ መሆኑ ተገልጿል። ተጠያቂነትን በማስፈን ይህንኑ ክፍተት ሊሞላ ይችላል ተብሎ የታመነበት ሀገራዊው የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ሕግ ጸድቆ በአፋጣኝ ወደ ሥራ ሊገባ ይገባል ተብሏል። በተካሄዱት ሁለት የፓናል ውይይቶች ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች በልዩ ሁኔታ በአካል ጉዳተኞችና በአረጋውያን ላይ የሚደርሰው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የከፋ እንዲሆን ያደረገው መሆኑ ተመላክቷል፡፡ በመሆኑም ለሰላም የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ተብሏል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ ኮሚሽኑ በዓመታዊ ሪፖርቱ ያቀረባቸው ምክረ ሐሳቦችን ሙሉ ተፈጻሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል። አክለውም የሚካሄዱ የውትወታ ሥራዎችን በአጋርነት መምራት የሚኖረውን ፋይዳ በማስታወስ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶችን ለማስጠበቅ እና ለማስፋፋት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።