የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙለትን ምክትል ዋና ኮሚሽነር እና የዘርፍ ኮሚሽነሮች ከሠራተኞች እና ከአጋር አካላት ጋር የማስተዋወቂያ መርኃ ግብር ሚያዚያ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት አካሂዷል። በመርኃ ግብሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና አባላትን ጨምሮ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል የኑስ ሙሉ፣ ጥሪ የተደረገላቸው አጋር አካላት እና የኢሰመኮ ሠራተኞች ተገኝተዋል።



በመርኃ ግብሩ ላይ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ፣ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር አሸነፈች አበበ፣ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ስልጠና ኮሚሽነር በዳሳ ለሜሳ፣ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር አቶ መሀመድ አህመድ ዝርዝር የሙያ፣ የክህሎት እና የትምህርት መግለጫ ቀርቧል። ተሳታፊዎች በበኩላቸው በገለልተኛ አስመራጭ ኮሚቴ አማካኝነት ግልጽ የሆነ የሕዝብ ጥቆማና የመመልመያ ሂደትን ተከትሎ ለተሾሙ ኮሚሽነሮች ደስታቸውን ገልጸው ውጤታማ የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።


በተጨማሪም በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ኮሚቴ (CESCR) እና በአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደኅንነት የባለሙያዎች ኮሚቴ (ACERWC) አባልነት ተመርጠው ለሀገራቸውና ለኢሰመኮ ኩራት ለሆኑት የሥራ ባልደረቦች ዶ/ር አብዲ ጅብሪል እና አልባብ ተስፋዬ የእውቅና እና የእንኳን ደስ አላችሁ መርኃ ግብር ተከናውኗል።



የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል የኑስ ሙሉ ክፍት የነበሩ የአመራር ቦታዎች ዘርፉን በአግባቡ በሚረዱ ባለሙያዎች መሞላታቸው ኢሰመኮ በተሟላ ዐቅሙ ተቋማዊ ተልዕኮውን እንዲወጣ ያስችለዋል ብለዋል። አክለውም የሰብአዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ሥራ በአንድ ተቋም ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ፣ በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሰዎችን መብቶች በተሟላ ሁኔታ ለማረጋገጥ ከኢሰመኮ ጋር በቅርበት እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ እውነቱ አለነ፣ ተሿሚዎቹ መስፈርቱን ካሟሉ 72 ዕጩዎች መካከል በከፍተኛ ውድድር እንደተመረጡ አስረድተዋል። የሰብአዊ መብቶችን መጠበቅ እና ማስፋፋት “ለራሳችን ስንል የምንሠራው ሥራ ነው” ያሉት ሰብሳቢው፤ ምክር ቤቱ የኢሰመኮን ተቋማዊ ነጻነት እና ገለልተኝነት ጠብቆ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ተሿሚዎቹም የሕዝብ እና የመንግሥትን አደራ በሕግ እና በመርሕ ላይ በመጽናት እንዲወጡ አሳስበዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ አብዛኛዎቹ ተሿሚዎች በኢሰመኮ ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ የነበሩ መሆናቸው ለተቋሙ ተጨማሪ ዐቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል። ይህም ተቋሙ በሰብአዊ መብቶች ዘርፍ ለበርካታ አመራሮችና ባለሙያዎች መፍለቂያ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ተስፋ ሰጪ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም፤ በሥራ ዘመናቸው ኢሰመኮ ነጻነቱን ጠብቆ፣ የሰብአዊ መብቶች ማስከበር ተግባሩ ተጠናክሮ እና የሚሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች ተፈጻሚነት ተሻሽሎ ማየት ዋነኛ ዓላማቸው መሆኑን ገልጸው፣ ተሿሚ ኮሚሽነሮች ይህንን እውን ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ መክረዋል።