የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2017 ዓ.ም. ያለውን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን፣ የሴቶች እና ሕፃናት እንዲሁም የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሁኔታ የተመለከቱ 4 ዓመታዊ የዘርፍ ሪፖርቶችን ዛሬ ይፋ አድርጓል። ኢሰመኮ ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታውን ጠቅለል ባለ መልኩ ያቀረበበትን አራተኛውን ዓመታዊ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረጉት 4 የዘርፍ ሪፖርቶች በየዘርፉ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተናጠል በዝርዝር የሚያመላክቱ ናቸው።
በዘርፍ ሪፖርቶቹ ውስጥ የተካተቱ ግኝቶች፣ ኢሰመኮ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎችን እንዲሁም የመቋቋሚያ አዋጁን መሠረት በማድረግ በራሱ አነሳሽነት እና በቀረቡለት አቤቱታዎች መነሻነት ባከናወናቸው ልዩ ልዩ ምርመራዎች፣ የሰብአዊ መብቶች ክትትሎች፣ የምክክር መድረኮች፣ ጥናትና ምርምሮች እንዲሁም በሰነዶች ትንተና አማካኝነት ባሰባሰባቸው መረጃዎች እና ማስረጃዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ኢሰመኮ የሚጠቀምባቸውን እና በሌሎች ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት እንዲሁም በዓለም አቀፍ አጣሪ ኮሚሽኖች ወይም እውነት አፈላላጊ አካላት ለሰብአዊ መብቶች ምርመራና ክትትል ሥራዎች ጥቅም ላይ የሚውሉ የማስረጃ ምዘና መስፈርቶችን (standard of proof) ያሟሉ ናቸው።
ዓመታዊ የዘርፍ ሪፖርቶቹ በ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን፣ በሴቶች እና ሕፃናት እንዲሁም በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ረገድ የታዩ ቁልፍ እመርታዎችን፣ አሳሳቢ ሁኔታዎችን እና ምክረ ሐሳቦችን በዝርዝር አካተዋል።
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ካመላከታቸው ቁልፍ እመርታዎች መካከል፣ በኅዳር ወር 2017 ዓ.ም. ለሀገር ውስጥ መፈናቀል ዘላቂ መፍትሔ ለማፈለላግ በብሔራዊ ደረጃ እንዲሁም በአፋር፣ አማራ፣ ሶማሊ እና ትግራይ ክልሎች ደረጃ ስትራቴጂዎች መዘጋጀታቸውና አስፈጻሚ የሥራ ቡድኖች መዋቀራቸው፤ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ መርኃ ግብር ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጋቸው ተጠቅሰዋል። በሌላ በኩል የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ እና በሕግ በግልጽ ሥልጣን የተሰጠው ተቋም አለመኖር ተፈናቃዮች በተራዘመ የመፈናቀል ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩ አስተዋጽዖ ማድረጉ፤ ወቅቱን የጠበቀ፣ ተደራሽ እና ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተፈናቃዮች ያማከለ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲሁም ትምህርትና ጤናን ጨምሮ የተሟላ ማኅበራዊ አገልግሎት የማይቀርብ መሆኑና በመጠለያ ጣቢያዎች፣ ተፈናቃዮች በተመለሱባቸው/ አዲስ በሰፈሩባቸው ቦታዎች የተሟላ ጸጥታ እና ደኅንነት ባለመኖሩ ተፈናቃዮች ድጋሚ መፈናቀልን ጨምሮ ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መጋለጣቸው በዘርፍ ሪፖርቱ ከተካተቱ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ናቸው።
የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት በበጀት ዓመቱ ለኢሰመኮ የውትወታ ሥራዎች አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ እርምጃዎች በየዘርፉ የተወሰዱ መሆኑን ያመላከተ ሲሆን፣ ለአብነትም ለአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ጥበቃና መስፋፋት እገዛ የሚያደርጉ አስቻይ የሕግ ማዕቀፎች ዝግጅት እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የመንግሥት እና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሕንጻ ተደራሽነት ችግሮችን ለማስተካከል እርምጃዎች መወሰዳቸው ተጠቅሰዋል። በአንጻሩ ግጭቶች በቀጠሉባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ላይ ጥቃቶች የሚፈጸሙ መሆኑ፤ በተለይም የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው እና መስማት የተሳናቸው ሰዎች በግጭት ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች የሚደርስባቸው ጥቃት መቀጠሉ እንዲሁም የአረጋውያን እንክብካቤ ማእከላት በግጭቶች ሳቢያ ዐቅማቸው መዳከሙ በሪፖርቱ አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከል ተካተዋል።
የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ካካተታቸው አበረታች እርምጃዎች መካከል የፍትሕ ሚኒስቴር በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አተገባበር ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ የተጎጂዎችና ተጋላጭ የማኀበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ስትራቴጂን ማርቀቁ፤ የአፋር ክልል ረቂቅ የቤተሰብ ሕግ ድንጋጌዎች ከሰብአዊ መብቶች መርሖች እና መመዘኛዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ መሻሻላቸው እንዲሁም በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሴት ልጅ ግርዛት በመፈጸም የተጠረጠሩ ሰዎች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉ ይጠቀሳሉ። በሌላ በኩል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግርዛትን ጨምሮ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ በሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሳቢያ በርካታ ሴቶች እና ሕፃናት ለተለያዩ ውስብስብ የጤና ጉዳቶች እንዲሁም ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች እየተዳረጉ መቀጠላቸው እንዲሁም የፍትሕ እና የአንድ ማእከል አገልግሎት ተቋማት የቋንቋ፣ አካላዊና የመረጃ ተደራሽነት ችግር ያሉባቸው በመሆኑ ምክንያት በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የሚያልፉ የጥቃት ተጎጂ ሴቶች እና ሕፃናት ለዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና ሥጋቶች የተጋለጡ መሆናቸው ተመላክቷል።
በበጀት ዓመቱ ጸድቀው ሥራ ላይ የዋሉ የጤና አገልግሎት፣ የትምህርት፣ የንብረት ታክስ እና የሕንጻ አዋጆች ለተለያዩ ሰብአዊ መብቶች ዝርዝር ዕውቅና ከመስጠት በተጨማሪ፣ የአካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ሕፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ የተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች መብቶች ጥበቃን የሚያጠናክሩ መሆናቸው እንዲሁም የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች ብሔራዊ የድርጊት መርኃ ግብር ዝግጅት ተጠናክሮ መቀጠሉ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ተገልጿል። ግጭቶች በቀጠሉባቸው አካባቢዎች ብዙ ቁጥር ያላቸው የጤና እና የትምህርት ተቋማት በመውደማቸው አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውና በዚህም በርካታ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ የወባ፣ ኮሌራና ኩፍኝ ወረርሽኞች ብዙ ሰዎች ተጎጂ መሆናቸው እንዲሁም የሠራተኞች ደመወዝ በወቅቱና በአግባቡ ባለመከፈሉ ምክንያት ሠራተኞች ለተለያዩ ችግሮች መዳረጋቸው በአሳሳቢነት ከተገለጹ ጉዳዮች መካከል ናቸው።
ኢሰመኮ ይፋ ያደረጋቸው የዘርፍ ሪፖርቶች ግኝቶችን መሠረት ያደረጉ ዝርዝር ምክረ ሐሳቦችን በማቅረብ፣ አበረታች ሁኔታዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉበትን እንዲሁም አሳሳቢ ጉዳዮች ፈጣን፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ የሚያመላክቱ ናቸው።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ኢሰመኮ ይፋ ያደረጋቸው የዘርፍ ሪፖርቶች ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታውን በጉልህ ማሳያዎች አማካኝነት በዝርዝር የሰነዱ መሆናቸውን አንስተው፤ የፖሊሲ፣ የሕግና የአሠራር ማሻሻያ እርምጃዎችን ተግባራዊ በማድረግ በሪፖርቶቹ የተመላከቱ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን እልባት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል። በተለይም መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን የማክበር፣ የማስከበር (የመጠበቅ) እና የማሟላት ባለግዴታ መሆኑን በመጥቀስ፣ ኢሰመኮ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ደረጃ የጀመራቸውን የውትወታ ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። አክለውም፣ በሂደት ላይ የሚገኙት የሽግግር ፍትሕ እና የሀገራዊ ምክክር ጥረቶች በኢሰመኮ ሪፖርቶችና የውትወታ መድረኮች አማካኝነት በተደጋጋሚ የሚነሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን፣ ሥጋቶችን እና መነሻ ምክንያቶችን በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት በሚችሉበት አግባብ መከናወናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸው፣ ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።