የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለአራተኛ ጊዜ ለሚያካሄደው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር ከክልል እና ከከተማ አስተዳደሮች ትምህርት ቢሮ አስተባባሪዎች ጋር የካቲት 14 እና 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የማስጀመሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የትምህርት ቢሮ አስተባባሪዎች እንዲሁም በ2015 ዓ.ም. በተካሄደው የ3ኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር አሸናፊ ተማሪዎች ተሳትፈዋል።
በኢሰመኮ አዘጋጅነት በየዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች የምስለ ችሎት ውድድር ምናባዊ በሆነ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ በመነሳት ተማሪዎች የአመልካች እና ተጠሪ ወገንን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር የሚያደርጉበት፤ ከሞላ ጎደል የመደበኛ ፍርድ ቤት የክርክር ሥርዓትን የሚከተል ወድድር ሲሆን በተወዳዳሪ ተማሪዎች እና በትምህርት ቤት ማኅበረሰብ ዘንድ የሰብአዊ መብቶች ዕውቀትን እና ክህሎትን ለመገንባት፣ አመለካከትን እና ባሕርይን ለመቅረጽ ያለመ ነው፡፡
በውይይቱ በጽሑፍ ክርክር፣ በቃል ክርክር፣ በውድድሩ መመሪያዎች እና በአስተባባሪዎች ሚና ላይ ገለጻ እና ውይይት ተደርጓል፡፡ ቀደም ሲል በተካሄዱ የምስለ ችሎት ውድድሮች ላይ በተከታታይ በመሳትፍ ውጤታማ የሆኑ እንዲሁም በዓመታዊ ዕቅዶቻቸው ውስጥ ውድድሩን አካተው የያዙ የትምህርት ቢሮዎች ተሞክሯቸውን አጋርተዋል፡፡ በተጨማሪም ሰብአዊ መብቶችን በተጓዳኝ መንገድ ለማስተማር ብሎም በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል ለሚካሄደው የሰብአዊ መብቶች የምስለ ችሎት ውድድር መሠረት ለመጣል የሰብአዊ መብቶች ክበባትን መመሥረት ስለሚኖረው ፋይዳ፤ እንዲሁም የተጓዳኝ ትምህርት ምንነት፣ ጠቀሜታ፣ አደረጃጀት እና አተገባበርን በተመለከተ ከትምህርት ሚኒስቴር በመጡ ባለሙያ እና በሰብአዊ መብቶች ትምህርት ሥራ ክፍል ባለሙያዎች ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ክበባቱን ለማቋቋም የሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎች እና አስፈላጊ ስለሆኑ ጉዳዮች ውይይት ተደርጓል፡፡
ኢሰመኮ በየዓመቱ የሚያካሄደው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምስለ ችሎት ውድድር ኮሚሽኑ ሰብአዊ መብቶችን ለማስፋፋት ከሚጠቀምባቸው መንገዶች መካከል አንደኛው እና ዋነኛው መሆኑን በመጥቀስ በዚህ ውድድር ልጆች ከለጋ ዕድሜያችው ጀምሮ ስለሰብአዊ መብቶች ዕውቀት የሚያገኙበት ብቻ ሳይሆን ባሕርያቸውም የሚታነጽበት መሆኑ በውይይቱ ተመላክቷል።
በውይይቱ አራተኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር የሚከናወንበት የጊዜ ሰሌዳ እና ዝርዝር ተግባራት ላይ ውይይት ተደርጎ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በውድድሩ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ እንደሚገባም ተገልጿል።
የሲቪል፣ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል “የሰብአዊ መብቶች የምስለ ችሎት ውድድርን ማካሄድ የሰብአዊ መብቶች ባህልን በተማሪዎች እና በትምህርት ማኅበረሰብ ዘንድ ለማጎልበት ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ኢሰመኮ ከትምህርት ቢሮዎች እና ከትምህርት ቤቶች ጋር በትብብር የሚሠራበት ዐይነተኛ መንገድ ነው ብለዋል”።
ውድድሩ በየዓመቱ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙርያ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን የዚህ ዓመት ውድድር ምናባዊ ጉዳይ “በሽግግር ፍትሕ ሂደት በሚነሱ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች” ላይ እንደሚያተኩር ይፋ ተደርጓል።