በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተሰየመው ዓለም አቀፍ የአልቢኒዝም ግንዛቤ ቀን እ.ኤ.አ. በየዓመቱ ጁን 13 ወይም ሰኔ 6 ቀን ታስቦ ይውላል። ዕለቱ አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች (persons with albinism) የሚደርስባቸውን መገለልና ዓይነተ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አስመልክቶ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው።

አልቢኒዝም ምንድን ነው?

አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች (persons with albinism) ብዙ ሰዎች ካላቸው የተለየ ነጣ ያለ የጸጉር፣ የቆዳ ወይም የዐይን ቀለም ያላቸውን ሰዎች ለማመላከት የሚውል አገላለጽ ነው። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚከሰተው የጸጉርን፣ የቆዳን ወይም የዐይንን ቀለም የሚወስነው የሜላኒን ቅንጣት በቆዳ ሕብረ ሕዋሳት ውስጥ አንሶ ወይም ጨርሶውኑ ሳይኖር ሲቀር ነው። አልቢኒዝም በዘረመል ልዋጤ (gene mutation) የሚከሰት እንደመሆኑ፤ በሁሉም የዓለም ሀገራት ባሉ የሰው ልጆች ላይ ሊፈጠር የሚችል ሁኔታ ነው።

በአጠቃላይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ከ5,000 ሰዎች ውስጥ አንዱ እንዲሁም በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ ከ20,000 ሰዎች ውስጥ አንዱ አልቢኒዝም እንዳለበት ይገመታል።[1] ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ ወቅታዊ መረጃ ባይኖርም እንደሌሎች የዓለም እና የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥም አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች አሉ።

አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?

አልቢኒዝም በራሱ ከሚያስከትለው ዓይነተ ብዙ ጫና አልፎ ለዐይነ ስውርነት ወይም በፀሐይ ኃይል (ultraviolet rays) ምክንያት ለሚከሰት የቆዳ ካንሰር ሊያጋልጥ የሚችል ሁኔታ ነው። አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች እንደ ማንኛውም ሰው የመማር፣ የመሥራት፣ ማኅበራዊ ተሳትፎ የማድረግ እና በቂ እና ደረጃውን የጠበቀ ሕይወት የመኖር መብት ያላቸው ቢሆንም በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ስለ አልቢኒዝም ባለ የተሳሳተ እምነት እና ማኅበረሰባዊ ልማዶች ሳቢያ አካላዊ ገጽታቸውን መሠረት ላደረጉ ዓይነተ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ይዳረጋሉ። ይህን ተጋላጭነታቸውን ታሳቢ በማድረግና ሁኔታው ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ በማለም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት እ.ኤ.አ. በሚያዝያ ወር 2015 አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ተከታታይ ገለልተኛ ባለሞያ (Independent Expert)[2] መድቧል።

አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች ከሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች መካከል ቀዳሚው መገለል እና አድልዎ (stigma and discrimination) ነው። አልቢኒዝም ‘‘በንክኪ ተላላፊ ነው’’ በሚል የተሳሳተ እምነት ምክንያት በመሰል ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን የማግለል ልማዶች በሰፊው ይታያሉ።[3] በአንዳንድ አካባቢዎች አልቢኒዝም ያለባቸውን ሰዎች ‘‘ከሰው ባሕርይ ውጪ የሆኑ’’ እና ‘‘በማኅበረሰብ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚያስችል የተለየ ኃይል ያላቸው’’ አድርጎ የማየት፤ አለፍ ሲልም አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎችን የሰውነት ክፍሎች በአምልኮ ሥርዓቶች ውስጥ መጠቀም “ሀብት ወይም ንብረት ሊያስገኝ ይችላል’’ የሚሉና መሰል የተሳሳቱ እምነቶችም አሉ። ከዚህም አልፎ አልቢኒዝም ካለባቸው ሰዎች ጋር ጋብቻ መመሥረት ‘‘መጥፎ እድል ያመጣል’’ በሚል ስር የሰደደ እምነት ሳቢያ ጋብቻና ቤተሰብ ለመመስረት ይቸገራሉ፤[4] አልቢኒዝም ያለባቸው ሴቶች ደግሞ ቢያገቡም እንኳን ለቤት ውስጥ ጥቃት ይበልጥ ተጋላጭ ሲሆኑ ይስተዋላል።

አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች ላይ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ከራሳቸውም አልፎ በቤተሰቦቻቸው ላይም ይደርሳል። ከእነዚህም መካከል አልቢኒዝም ያለባቸው ሕጻናት ወላጆች በልጆቻቸው አካል ላይ ለሚታየው ሁኔታ ‘‘ተወቃሽ/ተጠያቂ እንደሆኑ’’፣ ‘‘በፈጣሪያቸው የተረገሙ ወይም በፈጸሙት ኃጢያት ምክንያት እየተቀጡ እንደሆነ’’ የማመን ልማድ ይስተዋላል።[5] በዚህም ምክንያት ልጆችን የመተው (child abandonment) ወይም የጨቅላ ሕፃናት ግድያ (infanticide) የመሳሰሉ ድርጊቶች እንዲከሰቱ ያደርጋል።

አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች የሚያጋጥማቸው ሌላኛው ተግዳሮት የጥላቻ ወንጀሎች ናቸው። በተለይም ከመንፈሳዊ አምልኮ ጋር ተያይዞ የሚከናወኑ ጥቃቶች፣ በሕይወት የሌሉም ሆነ በሕይወት ያሉ አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች የሰውነት አካላትን መቁረጥ፣ መነገድ፣ እንዲሁም አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች ሕገወጥ ዝውውር በተለያዩ ሀገራት የተንሰራፋ የጥላቻ ወንጀል ዓይነት ነው።[6] ለዚህ ዓይነቱ የወንጀል ድርጊቶች ሁሉም አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች ተጋላጭ ቢሆኑም የሕፃናት ተጋላጭነት የከፋ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ገለልተኛ ባለሞያ ሪፖርት ያሳያል።[7] 

አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች ለሚያጋጥማቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ጥበቃ የሚያደርጉ የሕግ ማዕቀፎች የትኞቹ ናቸው?

በመሠረቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችም ሆኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአፍሪካ ኅብረት የወጡ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ለማንኛውም ሰው እኩል የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ የሚያደርጉ ናቸው። ለአብነት፦ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 25 “ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን፤ በዚህ ረገድ በዘር፣ በብሔር፣ ብሔረሰብ፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኀበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት’’ እንዳላቸው እውቅና ይሰጣል።

በተመሳሳይ፣ በሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 2 መሠረት ስምምነቱን የተቀበለ ሀገር በግዛቱ ውስጥ ለሚኖርና በስሩ ለሚተዳደር ማንኛውም ግለሰብ በዘር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም ሌላ አመለካከት፤ በብሔራዊም ሆነ ማኅበራዊ አመጣጡ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ መለኪያ ምንም ልዩነት ሳያደርግ በሕግ ዕውቅና ያገኙትን መብቶች የማስከበር እና የማረጋገጥ ግዴታ አለበት።

ይኸው የእኩልነት እና ከአድልዎ የመጠበቅ መብት አትዮጵያ አባል በሆነችበት የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ባህል መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን ዕውቅና አለው። በተጨማሪም ቃል ኪዳኑ ማንኛውም ሰው ሊደረስበት ወደሚችል ከፍተኛ የአካልና የአእምሮ ጤንነት ወደ ተሟላበት የኑሮ ደረጃ የመድረስ መብት ያለው መሆኑን በአንቀጽ 12 ስር ያስቀምጣል። ይህ ድንጋጌ በተለይም አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች ከሰውነታቸው የቆዳ ተፈጥሮ ጋር በተገናኘ ለቆዳ ካንሰር ሕመም ተጋላጭ እንደመሆናቸው ከፍተኛውን የጤና ደረጃ የማግኘት መብታቸውን ለማሟላት ወሳኝነት አለው። ከዚህም ባሻገር የተመድ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የባህል መብቶች ኮሚቴ በአጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 14 በሰጠው ማብራሪያ መሠረት “ከግለሰብ ጤና ጋር በተያያዘ የዘረመል ምክንያቶች” ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ በማስገንዘብ “ከፍተኛውን የጤና ደረጃ ለማሳካት የሚያስፈልጉ የተለያዩ መገልገያዎችን፣ ቁሶችን፣ አገልግሎቶችን እና ሁኔታዎችን የመጠቀም መብት የጤና መብት አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል” በማለት ገልጿል። በተያያዘም ትንታኔው የመንግሥትም ሆኑ የግል የጤና አገልግሎት ሰጪዎችና ተቋማት አካል ጉዳትን መሠረት ያደረገ አድልዎ እንዳይፈጽሙ አፅንዖት ሰጥቷል።

አሕጉራዊው የአፍሪካ የሰዎች እና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀጽ 2 “ማንኛውም ሰው በዘር፣ በጎሣ፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አስተሳሰብ፣ በብሔርና በማኅበራዊ ምንጭ፣ በሀብት፣ በመወለድ ወይም በሌላ ሁኔታ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግበት [በቻርተሩ] ዕውቅናና ዋስትና ያገኙት መብቶችና ነጻነቶች ተጠቃሚ ይሆናል” በሚል ዕውቅና ይሰጣል። ቻርተሩን ተከትሎ የወጣው የአካል ጉዳተኞች መብቶች ፕሮቶኮል አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች የሚያጋጥማቸው ግድያ አሳሳቢ የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑን በመግቢያው አመላክቷል። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የስምምነቱ ፈራሚ ባትሆንም ፕሮቶኮሉ “እንደ ጥንቆላ፣ መተው/ትኩረት መንፈግ/ችላ ማለት፣ መደበቅ፣ የአምልኮ ግድያዎች ወይም የአካል ጉዳትን ከመጥፎ አጋጣሚዎች ጋር ማያያዝ ያሉ አካል ጉዳተኛ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዶችን ለመከላከልና ለማስወገድ ሁሉንም ተገቢ እርምጃዎች’’ ሊወሰዱ እንደሚገባ ያስቀምጣል። በተጨማሪም በአካል ጉዳተኞች ችሎታዎች፣ ቀለም ወይም ባህሪ ላይ ያተኮሩ አመለካከቶችን ለማስወገድ የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ ደንግጓል።

ከላይ የተጠቀሱት ማዕቀፎች እንደተጠበቁ ሆኖ አልቢኒዝም ላለባቸው ሰዎች በቀጥታ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችለው ሌላኛው የሕግ ማዕቀፍ የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ነው። በስምምነቱ አንቀጽ 8 መሠረት መንግሥታት ስለ አልቢኒዝም ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ እና ጎጂ ልማዶች ለመዋጋት እንዲሁም አልቢኒዝም ያለባቸውን ሰዎች ችሎታና አስተዋጽዖ ለማስተዋወቅ ግንዛቤ የማስፋፋት ግዴታ ተጥሎባቸዋል። የስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተለው የተመድ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚቴ የቀረበለትን የግል አቤቱታ መሰረት አድርጎ በሰጠው ትንታኔም አካል ጉዳተኝነት ጉዳት ያለበት ግለሰብ ማኅበረሰባዊ ወይም ከባቢያዊ ሁኔታን መሰረት አድርጎ ከሚፈጠር ተግዳሮት ጋር በሚኖር መስተጋብር የሚፈጠር ሁኔታ እንደመሆኑ፤ አልቢኒዝም በስምምነቱ አንቀጽ 1 ላይ በተደነገገው የአካል ጉዳተኝነት ትርጓሜ ስር የሚወድቅ መሆኑን አረጋግጧል።[8] በመሆኑም አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች በስምምነቱ ዕውቅና ያገኙ መብቶቻቸው ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አመላክቷል።

አልቢኒዝም ያለባቸውን ሰዎች መብቶች በተሟላ ሁኔታ ለማረጋገጥ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች ምንድን ናቸው?

በመሠረቱ መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን የማክበር፣ የመጠበቅ እና የማሟላት ግዴታ አለበት። እነዚህ አጠቃላይ ግዴታዎች አልቢኒዝም ላለባቸው ሰዎችም ተግባራዊ የሚደረጉ ቢሆንም፤ በተለይም ከላይ የተጠቀሱትን የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች መሠረት አድርገው አልቢኒዝም ላለባቸው ሰዎች በመንግሥታት ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎችን የሚያብራሩና ተጨባጭ መለኪያዎችን የያዙ የፖሊሲ ማዕቀፎች አሉ። ከእነዚህም መካከል የአፍሪካ አህጉራዊ የአልቢኒዝም የድርጊት መርኃ ግብር (2017–2021 እ.ኤ.አ.) በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ግዴታዎችን አስቀምጧል። በመርኃ ግብሩ የተካተቱን ግዴታዎች አፈጻጸማቸውን ለመለካት እንዲያስችለው የአፍሪካ ሕብረት አልቢኒዝም ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችንና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለማስቆም ካወጣው የድርጊት መርኃ-ግብር የአፈጻጸም ማዕቀፍ አንጻር እንደሚከተለው ተዳሥስዋል።

  • መከላከል (prevention) አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎችን ሰብአዊ መብቶች ለማስፋፋት በአልቢኒዝም ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ለማሻሻል እና ለማስረጽ መደበኛ ትምህርት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎች ማድረግ ቀዳሚው የመከላከል ርምጃ ነው። በዚህ ረገድ አልቢኒዝም ባለባቸው ሰዎች ላይ ጥቃት በሚደርስባቸው ሥፍራዎች ቀጥተኛ ትምህርት መስጠትን ጨምሮ የመምህራንን እና የልምድ አዋላጆችን ጨምሮ የጤና ባለሙያዎችን እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ዘርፎችን ሁሉ አቅም በመገንባት አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎችን ሰብአዊ መብቶች ማስጠበቅ ይገባል።[9] በተጨማሪም የአካል ጉዳተኞችን በተለይም አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎችን ስታቲስቲክስ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባለው የዋሽንግተን ቡድን የጥያቄ መምሪያዎች (Washington Group Questions) መሠረት በጾታ፣ በዕድሜ እና በሌሎች ሁኔታዎች መሰብሰብ፣ ማደረጃት እና ማሰራጨት አስፈላጊ ነው።[10] እንዲህ ዓይነቱ መረጃ በተለይም አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች ላይ ስለሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ የፍትሕ አማራጮች ሂደት እና ውጤታማነትን እንዲያካትት ይጠበቃል።
  • ጥበቃ (protection) የድርጊት መርኃ ግብሩ አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በባህላዊ ሂደቶች እና ሥርዓቶች ውስጥ የመሳተፍ መብታቸውን የሚያረጋግጡ ሕጎችና ፖሊሲዎችን ማውጣትን ጨምሮ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ከሌሎች ጋር በእኩል ደረጃ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ የሚያስችል የሕግ ችሎታን የሚያጠናክሩ እንዲሁም ከብዝበዛ፣ ከዓመፅ፣ ከበደል እና ከጭካኔ ጋር ከተገናኘ አያያዝ ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ የሕግ ማዕቀፎችን እንዲዘረጉ ይጠበቃል።[11]
  • ተጠያቂነት (accountability) አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች ላይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የፈጸሙ ሰዎችን ተጠያቂነት ከማረጋገጥ ባሻገር የጥቃት ሰለባዎች እና ቤተሰቦቻቸው ሕይወታቸውን እንደገና እንዲያቋቁሙ የማኅበረ ሥነ ልቦና፣ የሕክምና፣ የሕግ፣ የደኅንነት ድጋፎች እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም የፍትሕ ሥርዓቱ ተለይተው የሚታወቁ አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች ፍላጎቶችን በአፋጣኝ ለመፍታት የሚያስችሉ ቀለል ያሉ ሂደቶችን ያካተቱ እንዲሆኑ ማድረግ፤ አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች ከሌሎች ጋር እኩል በሆነ መንገድ ፍትሕ እንዲያገኙ ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑትን ሕግጋት፣ ፖሊሲዎች እና ልምዶች መከለስ፣ ማሻሻል ወይም መሰረዝ፤ እንዲሁም ተደራሽ እና በቀላሉ የሚገኝ በነፃ ወይም በተመጣጣኝ ክፍያ የሕግ ድጋፍ እና እርዳታ ማቅረብን የመሳሰሉ ርምጃዎች ተጠያቂነትን ለማረገጋገጥ ሊወሰዱ ከሚገባቸው ርምጃዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።[12]
  • እኩልነትና አድልዎ ለማድረግ (equality and non-discrimination) አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎችን እኩልነትን ለማረጋገጥ እና የሚደርስባቸው አድልዎ ለማስወገድ በተለይም የአካቶ ትምህርት እና የአካቶ ጤና መርኃ ግብሮችን ማስፋፋት ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል። ሀገራት አካቶ ትምህርትን ለማስፋፋት በተለየም አካታች፣ ፍትሐዊ እና ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽነትን የሚያሳድጉ፤ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ላሉ አልቢኒዝም ላለባቸው ሕፃናት በተለይም ዝቅተኛ ዕይታ ላላቸው ሕፃናት ዕይታቸውን ከፍ የሚያደርጉ አስፈላጊ ቴክኖሎጂ እና ድጋፍ በማቅረብ ተመጣጣኝ ማመቻቸት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪ አልቢኒዝም በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲያካተት እና መምህራን በዘርፉ ተገቢውን ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ ያስቀምጣል። አልቢኒዝም ያለባቸውን ሰዎች የጤና መብት ከማስጠበቅ አንጻር በተለይም በገጠር አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች መደበኛ የጤና ምርመራ እንዲያገኙ የማድረግ፤ እንደ የእይታ መርጃዎች፣ የፀሐይ መከላከያ ቅባቶች፣ ልብሶች እና የፀሐይ መነፅር ያሉ የጤና ድጋፍ፣ አገልግሎቶች እና የጤና ቁሳቁሶች ተደራሽነትን የማረጋገጥ፤ የቆዳ ካንሰር ሕክምናን የማስፋፋት እንዲሁም ለዝቅተኛ ዕይታና የቆዳ እንክብካቤ አገልግሎቶች ትኩረት የመስጠት ርምጃዎችን መወሰድ ያስፈልጋል።[13]

በአጠቃላይ አልቢኒዝም ያለባቸውን ሰዎች ሰብአዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ ለማስጠበቅ፣ ማኅበራዊ ተካታችነታቸውን ለማስፋፋት እና በጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች የሚያጋጥማቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማስወገድ ተጨባጭ እነዚህና ሌሎች ልዩ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ እርምጃዎች መውሰድ ይገባል።


1 United Nations, General Assembly, ‘Report on albinism worldwide’ (18 July 2019
https://docs.un.org/en/A/74/190

2 United Nations, General Assembly, ‘Independent Expert on the Enjoyment of Human Rights by
Persons with Albinism’ (10 April 2015) https://docs.un.org/en/A/HRC/RES/28/6

3 United Nations, General Assembly, ‘The right to health and persons with albinism in the context of
skin cancer: Report of the Independent Expert of persons with albinism’ (22 July 2025) https://www.ohchr.org/en/documents/thematic-reports/a80222-right-health-and-personsalbinism-context-skin-cancer-report

4 United Nations General Assembly, ‘Addressing Attitudinal Barriers Experienced by Persons with
Albinism: Report by the Independent Expert on the Rights of Persons with Albinism’ (16 July 2021)
https://digitallibrary.un.org/record/3968727/files/A_76_769-EN.pdf

5 Ibid.

6 United Nations General Assembly, ‘Report of the Independent Expert on the Enjoyment of Human
Rights by Persons with Albinism’ (10 January 2017) https://docs.un.org/en/A/HRC/34/59

7 Ibid.

8 Y v. United Republic of Tanzania, Communication No. 23/2014, U.N. Doc. CRPD/C/20/D/23/2014
(2018), Para 7.5, https://docs.un.org/en/CRPD/C/20/D/23/2014

9 African Union, ‘Implementation Matrix of the Plan of Action to End Attacks and Other Human
Rights Violations Targeting Persons with Albinism in Africa (2021–2031)’ 4.

10 Ibid 13. See also Artcile 31 of the Cnvention on the Rights of Persons with Disabilities

11 Ibid 19 – 20.

12 Ibid 21 – 33.

13 Ibid 35 – 37.