የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሃዋሳ ከተማ ዙሪያ በሴት ሕፃናት ላይ በሚፈጸሙ የጠለፋ እና ሌሎች ጎጂ ድርጊቶች ያስከተሉትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በተመለከተ በሲዳማ ክልል 7 ወረዳዎች ከተውጣጡ የክልሉ ሴት የሕፃናት ፓርላማ ተወካዮች ጋር በጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በሃዋሳ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይቱ በሃዋሳ ከተማ ዙሪያ በሴት ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ የጠለፋ እና ሌሎች ጎጂ ድርጊቶች ያስከተሉት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በምን ደረጃ ላይ እንዳለ፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ድርጊቶቹን ለመከላከልና የወንጀል ፈጻሚዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ያከናወናቸው ሥራዎች እና የታዩት ክፍተቶች እንዲሁም በዚህ ረገድ የሲዳማ ክልል ሕፃናት ፓርላማ ሚና ምን መሆን አለበት የሚሉት ዋና ዋና የመወያያ ነጥቦች ነበሩ፡፡
በዚህም መሰረት ጠለፋ እና ሌሎች ጥቃቶች በሃዋሳ ከተማ ዙሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸው፣ በፍርድ ቤት የሚሰጡ ውሳኔዎች እስከ መጨረሻ አለመፈጸማቸው እና የወንጀል ምርመራ ከተጀመረ እንዲሁም ክስ ከተመሰረተ በኋላ ሂደቱ ተቋርጦ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲያልቅ መደረጉ ከተጠቆሙ ክፍተቶች መካከል ናቸው። የሀገር ሽማግሌዎች የጠለፋ እና ሌሎች ጎጂ ድርጊቶች ተፈጽመው ሲገኙ ጉዳዩ በባሕላዊ የዕርቅ ሥርዓት እንዲፈታ ከፍተኛ ግፊት ማድረጋቸው እና ጣልቃ መግባታቸው እንዲሁም የወንጀል ምርመራ ወይም ክስ እንዲቋረጥ በሚያደርጉ የሕግ አስፈጻሚ አካላት ላይ የሥነ-ምግባር እርምጃ እንዲወሰድ አለመደረጉ በዋናነት ተለይተው ከተነሱ ችግሮች መካከል ነበሩ፡፡ ለክልሉ የሕፃናት ፓርላማ የሕፃናት መብቶች ጥሰቶች ጥቆማ መድረሱና ተጎጂዎችም ፍትሕ እንዲያገኙ የተደረገው ጥረት አበረታች ቢሆንም የበለጠ መሥራት እንደሚገባ የፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል።
በመጨረሻም የሕፃናት መብቶችንና ጥቅሞችን በሚመለከት እና የሰብአዊ መብቶች ሥራዎች የሕፃናትን ጥቅም በቅድሚያ ያማከሉ እንዲሆኑ የሕፃናት ፓርላማ ተወካዮቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡