የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አካታች እና ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ የሽግግር ፍትሕ ሂደትን እውን ለማድረግ የሚያግዝ የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ኮንሶርትየም/ጥምረት (Transitional Justice Consortium- Ethiopia) ጋር ሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ተፈራርሟል። ስምምነቱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ እና የጥምረቱ ተወካይ የአፍሪካ የሽግግር ጥናት ማዕከል ዋና ዳይሬከተር ሙሉቀን ጌታቸው የተፈራረሙ ሲሆን፣ ስምምነቱ ኢሰመኮ ከተቋሙ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት በመሥራት፣ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ የሽግግር ፍትሕ እንዲተገበር ለሚያደርጋቸው ጥረቶች ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።

በአራት ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማለትም የአፍሪካ የሽግግር ጥናት ማዕከል (African Center for Transitions Studies- ACT)፣ የአርብቶ አደሮች ልማት አጋርነት (Partnership for Pastorialists Development – PAPDA)፣ የኢትዮጵያ የሰላም ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት (Consortium for Ethiopian Civil Society Organizations of Peace – CESCOP)፣ እና የአፍሪካ ቀንድ የዴሞክራሲ ማዕከል (Horn Center for Democracy – HCD) የተመሠረተው የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ኮንሶርትየም፣ በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተባባረ መልኩ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማስቻልን ዓላማው ያደረገ ነው።

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ጥምረቱን የወከሉት የአፍሪካ የሽግግር ጥናት ማዕከል ዋና ዳይሬከተር ሙሉቀን ጌታቸው የመግባቢያ ሰነዱ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ሁሉን አሳታፊ እንዲሆን ለሚደረጉ ጥረቶች መሳካት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸው፤ በመግባቢያ ስምምነቱ ለኮንሰርትየሙ የተፈቀደውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቅኝት እና ምደባ (CSO Mapping and categorization) ፕሮጀክት በተሻለ ትጋት ለመፈጸም ጥረት እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ስምምነቱ በኢትዮጵያ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፣ አካታች እና ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ የሽግግር ፍትሕ ሂደትን ለመተግበር አዎንታዊ አበርክቶ ያለው መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ኢሰመኮ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሽግግር ፍትሕ ዙርያ የዐቅም ግንባታ እና ተሳትፎን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ሲደግፍ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ይህ አጋርነት ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ያለውን የዘለቀ ትብብር ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።