የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (Office of the United Nations High Commissioner for Refugees-UNHCR) ፣ Jesuit Refugee Service (JRS) እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነጻ የሕግ ድጋፍ ማእከል ጋር በመተባበር ዓለም አቀፉን የስደተኞች ቀን “ሁሉም ሰው ደኅንነቱ እስኪረጋገጥ ድረስ” በሚል መሪ ቃል ሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አክብሯል። መርኃ ግብሩ የስደተኞችን ጽናት፣ አስተዋጽዖ እና ስኬቶችን ለማክበር፣ ስለ መብቶቻቸው ግንዛቤን ለማሳደግ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የስደተኞች ጥበቃ፣ ተሳትፎና አካታችነትን ለማጠናከር ያለመ ነው።

በመርኃ ግብሩ በስደተኞች በሚመሩ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ደኅንነቱ የተጠበቀ የስደተኞች ቦታ ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን የስደተኞች መር ድርጅቶች (Refugee-Led Organisations (RLOs)) ተወካዮች የመደራጀት መብት ለስደተኞች ተሳትፎና አመራር ያለውን አስፈላጊነት፣ ድርጅቶቻቸው ለስደተኞችና ለተቀባዩ ማኅበረሰብ የሚያበረክቱትን አስተዋጽዖ፣ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን እና ወደፊት የስደተኞችን ተሳትፎና አመራር ለማጠናከር ያሉ ዕድሎችን በሚመለከት ልምዳቸውን አጋርተዋል። በተጨማሪም የስደተኞች መብቶችን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች እና ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀንን ታሳቢ ያደረገ የከተማ ስደተኛ ተማሪዎች የተሳተፉበት የጥያቄና መልስ ውድድር ተካሂዷል።

በመርኃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መብቶች ጥበቃ ለማጠናከር፣ የጎላ ድምጽ እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት እና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።