የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በኅዳር ወር 2017 ዓ.ም. 3 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ እገዳ ማስተላለፉን ተከትሎ በቀረቡለት አቤቱታዎች እና በደረሰው መረጃ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ “ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ መሥራት ሲገባው ከዓላማው ውጭ በመንቀሳቀስ የሀገርን ጥቅም የሚጎዳ ተግባራት ላይ መሰማራቱ” የሚል የእገዳ ደብዳቤ የደረሳቸው መሆኑን ለመረዳት ችሏል። ኢሰመኮ ጉዳዩን በመከታተል ላይ እያለ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ተጨማሪ 2 በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተመሳሳይ ይዘት ባለው እና ተቋሟቱ የፈጸሟቸውን ከባድ የሕግ ጥሰቶች በዝርዝር ባላስቀመጠ ደብዳቤ መታገዳቸው አሳሳቢ ሆኖ አግኝቶታል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በኅዳር ወር 2017 ዓ.ም. የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማእከል፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች እና ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ የተባሉ 3 በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን አግዶ እንደነበር ይታወሳል። ባለሥልጣኑ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ በ3ቱም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የጣለውን እግድ አንስቶ የነበረ ቢሆንም ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በድጋሚ በጻፈው ደብዳቤ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማእከልን እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶችን ከማንኛውም እንቅስቃሴ ለ2ተኛ ጊዜ አግዷል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሠሩትን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማእከልን ማገዱን ገልጿል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚተላለፉ ተደጋጋሚ እገዳዎች የሲቪክ ምኅዳሩን በማጥበብ በማኅበር የመደራጀት መብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር ባለሥልጣኑ የድርጅቶቹን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ የምርመራ ሥራዎቹን በተቻለ ፍጥነት አጠናቆ ወደ ሥራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ኢሰመኮ ጥሪ ያቀርባል።