የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ አቶ ብርሃኑ አዴሎን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር አድርጎ ሾሟል። የዋና ኮሚሽነር ሹመት በኢሰመኮ ማቋቋሚያ አዋጅ 210/1992 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) አንቀጽ 10፣ 11 እና 12 በተደነገገው መሠረት የተካሄደ ነው።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት አቶ ብርሃኑ አዴሎ ከዚህ ቀደም በተለያዩ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር፣ እንዲሁም የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነበሩ።
የኢሰመኮ የቀድሞ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሥራ ዘመን መጠናቀቁን ተከትሎ ከሐምሌ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ኢሰመኮን በተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነርነት ራኬብ መሰለ፣ ዶ/ር አብዲ ጅብሪል በሲቪል፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በማኅበራዊ መብቶች ኮሚሽነርነት፣ እንዲሁም ርግበ ገብረሐዋሪያ በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነርነት ሲመሩ ቆይተዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ሹመቱን በማስመልከት ባስተላለፉት መልእክት ወቅታዊ የሀገሪቱ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ጠንካራ አመራር እና ውጤታማ የሰብአዊ መብቶች ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን በማስታወስ የኢሰመኮን ኮሚሽነሮች እና ባልደረባዎች በመወከል ለዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ ከወዲሁ “መልካም የሥራ ዘመን እመኝላቸዋለሁ” ብለዋል።