የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጎፋ ዞን፣ በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ የደረሰው የመሬት ናዳ አደጋን ተከትሎ በሰዎች ሕይወት ላይ፣ በመኖሪያዎቻቸው እና በመተዳደሪያዎቻቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የሚደርሱት ጥቆማዎች እና ሪፖርቶች በእጅጉ አሳሳቢ ናቸው።
የጎፋ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባሳወቀው መሠረት ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ ከ229 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ከእነዚህም መካከል 81 የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ በአጠቃላይ በአካባቢው ላይም ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ሆኖም የሟቾች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል እና የአፋጣኝ ምላሽ ሥራው እንደሚቀጥል መምሪያው አክሎ ገልጿል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና በዞኑ የመንግሥት አካላት ትብብር፣ በሀገራዊ የሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢ ድርጅቶች፣ እንዲሁም በአካባቢው ነዋሪዎች በወረዳው በድንገተኛ የናዳ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የተለያዩ ቁሳቁሶችን ጨምሮ የተወሰነ አፋጣኝ ድጋፍ መደረጉ አበረታች ነው። ሆኖም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰንዳይ የአደጋ ሥጋት ቅነሳ ማዕቀፍ (UN Sendai Framework for Disaster Risk Reduction, 2015-2030)፣ በአፍሪካ ሕብረት የሰንዳይ የአደጋ ሥጋት ቅነሳ ማዕቀፍ የተግባር መርኃ ግብር (Programme of Action for the Implementation of Sendai Framework for Disaster Risk Reduction in Africa, 2015-2030) እና በብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ መሠረት የሰብአዊ መብቶች መርሖችን እና ድንጋጌዎችን የሚያሟላ እንዲሆን ለማስቻል የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት አካላት እና ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች አፋጣኝ ርብርብ እንዲያደርጉ ኢሰመኮ ጥሪውን ያቀርባል።
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት አሳሳቢነት በማስታወስ “በተፈጥሮ አደጋ ወቅት በተለይም በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአረጋውያን እና በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰው ጉዳት የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ከግንዛቤ ውስጥ እንዲገባ፣ በዚሁ ክስተት ሳቢያ ከመኖሪያ ቦታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የተጠለሉ ሰዎች አፋጣኝ ድጋፍ እንዲደረግላቸው” ጥሪ አቅርበዋል።