የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሕገ መንግሥቱ እና በማቋቋሚያ አዋጁ በተሰጠው ሕጋዊ ሥልጣን መሠረት፣ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎችን የመከታተል፣ የመመርመር፣ ምክረ ሃሳብ የማቅረብ እና ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ የማስገንዘብ ጥረት የማድረግ ተልዕኮ ያለው ነጻና ገለልተኛ ብሔራዊ ተቋም ነው።

ኢሰመኮ በሚያወጣቸው ወቅታዊ ሪፖርቶች እና ምክረ ሃሳቦች በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ አለመግባባቶችና ልዩነቶች በሕጋዊ፣ በሰላማዊ መንገድና በድርድር እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ምክረ ሃሳቦችን ሲያቀርብ፣ በተግባርም እንዲፈፅም ያልተቋረጠ ጥረት ሲያደርግ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሰብአዊ መብቶችን ማስከበር እና ማስፋፋት የሚቻለው የኮሚሽኑን ነጻነት በጠበቀ መልኩ ከመንግስት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀራረብ በመስራት (constructive engagement) መሆኑን በማመን የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፤ በርካታ ውጤቶችም ተገኝተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ እና በሽብርና ሌሎች ከባባድ ወንጀሎች ተከሰው ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠባቸው፣  እንዲሁም በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ ዜጎች፣ ጉዳያቸው በልዩ ሁኔታ እንዲታይላቸው በኮሚሽኑ በኩል ለመንግሥት እንዲቀርብላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ፤ እንዲሁም በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶችን በማቀናጀት ኮሚሽኑ ጉዳዩን ለመንግሥት አቅርቧል።

ይህንኑ በክስ ሂደት ላይ የሚገኙ ወገኖች በራሳቸው ፍላጎት ያቀረቡትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ኮሚሽኑ ያቀረበውን ጉዳይ፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ምንጊዜም የሕግ የበላይነትን ባከበረ መልኩ ለሰላም፣ ለሀገራዊ መግባባት እና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚረዱ እርምጃዎችን ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆኑን በመግለፅ የቀረበውን ጉዳይ በአዎንታ በመቀበልና ኢሰመኮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል በመደገፍ፣ መንግሥት ይህንን ሀገራዊ የሰላም ግንባታ ሂደት በሕግ አግባብ በተግባር እንዲያስፈጽም ለሚመለከታቸው የመንግሥት መዋቅሮች ቁርጠኛ አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በተመሳሳይ መልኩ በክልል ደረጃ በሚታዩ ጉዳዮች ላይ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ተመሳሳይ ውሳኔ እና ቁርጠኝነት ወስደዋል።

በዚሁ መሠረት የተቀመጠው የሕግና የይቅርታ አሰራር ሂደትን ተከትሎ በተለያዩ ወንጀሎች የተፈረደባቸው በይቅርታ፤ በክስ ሂደት ላይ ያሉ ተከሳሾች በቅድመ ሁኔታ ክሳቸዉ ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ፤ ከክስ ሂደቱ ጋር በተያያዘ የተገደቡ መብቶቻቸው በሕግ መሠረት እንዲከብሩላቸው እና ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ የተወሰነውን ወሳኔ ኢሰመኮ አድናቆት የሚሰጠው እና ወደፊትም ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው፡፡ 

ኢሰመኮ መንግሥት ሀገራዊ ሰላምን፣ ሀገራዊ መግባባትን እና የዲሞክራሲ ስርዓትን ለማጠናከር ያከናወናቸውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት፦ ማለትም  የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን፣ የትጥቅ ማስፈታትና መልሶ ማቋቋም (DDR) ፕሮግራሞችን፣ በክልሎች የተደረጉ የሰላም ጥሪዎችን እንዲሁም ሕዝባዊ የሰላም ውይይቶችን በበጎነት ይመለከታል። በተጨማሪም ባለፉት 5 ወራት በኮሚሽኑ በኩል ለተደረገው ጥረት በሂደቱ ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ሁሉ እውቅና እየሰጠ፣ መንግሥት ይቅርታንና የሕግ አሰራርን መሠረት በማድረግ የወሰደው ይህ እርምጃ ለዘላቂ ሰላም፣ ለሀገራዊ መግባባት እና ለዲሞክራሲ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው እንደሆነ ያለውን እምነትም ያረጋግጣል።

ኮሚሽኑ በቀጣይም እነዚህን መንግሥት በተለይም ለሰላም ግንባታ የመፍትሔ ሂደቶች የወሰዳቸውን አዎንታዊ እርምጃዎችና ጥረቶች በቅርበት የሚከታተል እና ሂደቶቹ በሙሉ ሰብአዊ መብቶችን ባከበረና አካታች በሆነ መልኩ ተተግብረው ለዘላቂ ሰላም፣ ለፍትሕና ለተጠያቂነት መረጋገጥ ጠንካራ መሠረት እንዲሆኑ የክትትል ሪፖርት የማቅረብ ተግባራትን የሚያከናውን ሲሆን፣ ዘላቂ ሰላም ለሰብአዊ መብቶች በሁለንተናዊነት መከበር መሰረታዊ መሆኑን የሚያምን በመሆኑ ጥረቶቹ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳስባል፣ ለእስክ አሁኑ ጥረቶቹም እውቅና ይሰጣል፡፡

ኢሰመኮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ጥረት መንግስት ጥያቄውን ተቀብሎ ዜጎች ከእስር እንዲለቀቁ መወሰኑ ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ከመሆኑም በላይ ለሌላው ዓለም ምሳሌ የሚሆን እርምጃ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በድጋሚ ያረጋገጣል።

በመንግስት ውሳኔ መሰረት በዛሬው እለት ከ 600 በላይ ሰዎች ከእስር ተለቀዋል። ኮሚሽኑ በሂደቱ የነበረውን ከፍተኛ ጥረት መሰል ስራዎችም አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ለመግለፅ ይወዳል።ኮሚሽኑ መንግስት በወሰደው ቁርጠኛ አቋም እንዲሁም እስር ላይ የነበሩ ወገኖቻችን ለሂደቱ ስኬት ላሳዩት ዝግጁነት እና ለሂደቱ ውጤታማነት ለተረባረቡ ወገኖች በሙሉ ምስጋና ማቅረብ ይወዳል፡፡

በዛሬው እለት ከእስር የወጡ ዜጎች ወደየአካባቢያቸው በመመለስ በሀገራዊ የሰላም ግንባታ እና ልማት ተግባራት ላይ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ እንዲሳተፉ እና ከጸረ ሰላም ተግባራት እራሳቸውን እንዲያርቁ ኮሚሽኑ ያሳስባል። በየአካባቢው በተዋረድ የሚገኙ የመንግስት የአስተዳደር አካላት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች የሚመለከታቸው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከእስር የተለቀቁ ዜጎቻችንን በማቋቋም ወደ መደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲያግዙ ኢሰመኮ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ 

በዚህ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮች በትጥቅ ትግል እና በኃይል ይፈታል ብለው የሚያምኑ ኃይሎች ወደ ሰላምና  ድርድር እንዲመጡ ኢሰመኮ አሁንም በድጋሚ ምክረ ሃሳብ ያቀርባል።

በመጨረሻም በእስር ላይ የነበሩ ወገኖቻችን እንዲለቀቁ በመንግሥት እና በኮሚሽኑ የተደረገውን ጥረትና ውጤት ላልተገባ የፖለቲካ አጀንዳ፤ ለሰላምና ፀጥታ መደፍረስ ለማዋል የሚፈልጉ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ኮሚሽኑ ያሳስባል።