የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ግንባታው ተጠናቆ ለአስርት ዓመታት ወደ ሥራ ሳይገባ የቆየው የሰመራ የአካል ጉዳተኞች ተሐድሶ ማእከል አገልግሎት መስጠት መጀመር በሚችልበት ሁኔታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የውይይት መድረክ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰመራ ከተማ አካሂዷል። በውይይቱ የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎትን ጨምሮ የክልሉ ፕሬዚደንት ጽሕፈት ቤት፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የጤና ቢሮ፣ የአፋር አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች እና ሌሎች አጋር አካላት ተሳትፈዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

ኢሰመኮ በ2014 ዓ.ም. በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ የነበረው ግጭት በአፋር እና አማራ ክልሎች በሚኖሩ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ አስመልክቶ ክትትል በሚያካሂድበት ወቅት የሰመራ ተሐድሶ ማእከል ሁኔታን ለመገንዘብ የቻለ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎም ሚያዚያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ከአፋር ክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት አካሂዷል። በተጨማሪም በጷጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲሁም በጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ለ2ተኛ ጊዜ ይፋ ያደረጋቸው የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቶች ላይ የሰመራ የአካል ጉዳተኞች ተሐድሶ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ምክረ ሐሳቦቹን ለማስፈጸም በርካታ የውትወታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። እንዲሁም በጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ማእከሉ ያለበትን ሁኔታ በአካል በመገኘት ከክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ተመልክቷል፤ ውይይትም አካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በውይይቱም በክልሉ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና ጤና ቢሮ መካከል ባለው የይዞታ ይገባኛል ክርክር ምክንያት ማእከሉ እስከአሁን ድረስ ወደ ሥራ አለመግባቱ እና ያለጥቅም ተዘግቶ በመቆየቱ ቀድሞ ከነበረበት ሁኔታ በእጅጉ መጎዳቱን ኢሰመኮ በአካሄደው ምልከታ መገንዘቡ ተገልጿል። የክልሉ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች በበኩላቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በክልሉ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች የአካል ድጋፍ እና የተሐድሶ አገልግሎት ለማግኘት በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ ደሴ ከተማ ወደሚገኘው የደሴ የአካል ጉዳተኞች ተሐድሶ ማእከል እንደሚላኩ ጠቁመዋል። በዚህም ምክንያት በአየር ንብረት ለውጥ፣ የማኅበረ- ሥነልቦና ድጋፍ አለማግኘት እንዲሁም የአካባቢውን ምግብ አለመላመድ ጋር በተያያዘ አካል ጉዳተኞች ጤናቸው መስተጓጎሉ እና አገልግሎቱን በአግባቡ ማግኘት እንዳይችሉ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ተናግረዋል። በመጨረሻም ማእከሉን ወደ ሥራ ለማስገባት የክልሉን ፕሬዚደንት ጽሕፈት ቤት ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊያበረክቱ የሚችሏቸውን አስተዋጽዖዎች ያካተተ የድርጊት መርኃ ግብር ተዘጋጅቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

የኢሰመኮ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሜቲ አቶምሳ ኢሰመኮ ማእከሉ ሊሰጥ የሚገባውን አገልግሎት ለማስጀመር ከዚህ ቀደም ያደረጋቸውን ጥረቶች ጠቅሰው ይህ በርካታ የሕዝብ እና የመንግሥት ሀብት የፈሰሰበት ተቋም ከአስርት ዓመታት በላይ ለታለመለት ዓላማ አለመዋሉ በክልሉ አካል ጉዳተኞች ላይ እየፈጠረ ያለውን ጫና ከግምት በማስገባት ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። አክለውም ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት እስከሚጀምር ድረስ ኢሰመኮ የውትወታ ሥራውን አጠንክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።