የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እና የኮሚሽኑ ባለሙያዎች በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ስር የሚገኘው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በመገኘት በታሳሪዎች አያያዝ ሁኔታ ላይ ክትትል አድርጓል፡፡
አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ከእነርሱ ጋር ከተከሰሱት ውስጥ አቶ ሀምዛ ቦረና፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ ሸምሰዲን ጣሃ እና ጋዜጠኛ መለስ ድሪብሳን፤ እንዲሁም አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮልን ጨምሮ ከእነርሱጋር የተከሰሱትን ወ/ሮ ቀለብ ስዩም እና ወ/ት አስካለ ደምሌን፣ በተጨማሪም እነ ጄነራል ክንፈ ዳኘው እና ሌሎችምታሳሪዎችም የሚገኙበትን የእስር ሁኔታ ጐብኝተዋል፣ ታሳሪዎችንና ኃላፊዎችንም ለየብቻ አነጋግረዋል፡፡
በጉብኝቱም ታሳሪዎቹ በአካላዊ ደህንነት ላይ እንደሚገኙ፣ አጠቃላይ የእስር ቤቱ ሁኔታና የእስር አያያዝም ተቀባይነት ባለው ደረጃ መሆኑን ተመልክቷል፣ የተወሰኑ እስረኞች አስተዳደራዊ እልባት የሚሹ የተወሰኑ ጉዳዮች ከማንሳታቸው በስተቀር በእስር ቤቱ ሁኔታ ላይ ቅሬታ አልቀረበም፡፡
አስተዳደራዊ እልባት ከሚሹ የተወሰኑ ታሳሪዎች ቅሬታዎች ውስጥ የሕክምና አገልግሎትና የመድኃኒት አቅርቦት በሚፈለገው ፍጥነት አለመገኘቱ፣ ታሳሪዎች ለፍርድ ቤት ለመላክ የሚፈልጉት አቤቱታ በአፋጣኝ አለመላኩ፣ ለቤተሰብ ጉብኝት በቂ ጊዜ አለማግኘትና የስልክ አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ አለመዳረስ ይገኝበታል፡፡ በሌላ በኩል የአብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ዋነኛ አቤቱታ የጉዳያቸው በአፋጣኝና በፍትሃዊ መንገድ መታየት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ለኮሚሽኑ እንዳስረዱትም ለታሳሪዎች የሚያስፈልገውን አገልግሎት በተሟላ መንገድ ለማቅረብ ጥረት እንደሚደረግ፣ የቤተሰብ ጉብኝት ሰዓት በኮሮና በሽታ ምክንያት የጊዜ ገደብ ቢኖረውም እንደየሁኔታው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹ ያቀረቡትን አጠቃላይ አስተዳደር ነክ ቅሬታዎችና እንዲሁም የተወሰኑ ታሳሪዎችን የሚመለከቱ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ከማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት የማስተካከያ ምክረ ሀሳቦችን አቅርቧል፣ በመፍትሄ ሃሳቦቹም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡