የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሶማሊ ክልል በተመረጡ የአርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት መብት አተገባበርን አስመልክቶ ባከናወነው የሰብአዊ መብቶች ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ መጋቢት 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በጅግጅጋ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል። በውይይቱ ከሶማሊ ክልል ትምህርት ቢሮ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች፣ ሴቶችና ሕፃናት፣ አደጋ ሥጋት አመራር ቢሮዎች እንዲሁም ከተለያዩ የወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።



በመድረኩ ኢሰመኮ የትምህርት መብት በዓለም አቀፍና ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች የተሰጠውን ጥበቃ ጨምሮ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የመብቱ አተገባበር ላይ ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በውይይቱ በከፍተኛ ንፋስ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችን መልሶ መገንባት እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታን ማስፋፋት እንዲሁም የመምህራንን ዕውቀት እና ክህሎት ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው ስልጠና መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል። በተጨማሪም ተንቀሳቃሽ እና አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋትን ጨምሮ ከአርብቶ አደሩ የኑሮ ዘይቤ ጋር የሚጣጣሙ የትምህርት ስልቶችን መቀየስ አጽንዖት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡


የውይይቱ ተሳታፊዎች አርብቶ አደሮች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በዘላቂነት ለመፍታት በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኢሰመኮ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ኃላፊ ሃዊ አስፈው፣ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት መብትን ለማረጋገጥ ከማኅበረሰቡ የኑሮ ዘይቤ ጋር ማጣጣምና ተደራሽነቱን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም የመሠረተ ልማት ችግር እና ሌሎች ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርጉና የመፍትሔ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።