የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምርጫ ሂደት የሰብአዊ መብት ጥበቃን በሚመለከት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ምርጫ በሚካሄድባቸው ሁሉም ክልሎች ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር ከሰኔ 2 እስከ ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ምክክሮችን አከናውኗል። ምክክሮቹ የተከናወኑት ከአዳማ፣ ከጅማ፣ ከባሕር ዳር፣ ከሃዋሳ፣ ከጋምቤላ፣ ከአሶሳ እና ከሰመራ ከተሞች ፖሊስ እና የፍትህ አካላት ከተውጣጡ መካከለኛ አመራሮች ጋር ነው።
ኮሚሽኑ የምክክር መድረኮቹን ያከናወነው የሕግ አስከባሪ አካላት ካለባቸው ሰብአዊ መብቶችን የማክበር፣ የማስከበር እና የማሟላት ኃላፊነት አኳያ፣ በቅድመ ምርጫው፣ በምርጫው ዕለትና በድኅረ-ምርጫው ወቅት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ የሕግ አስከባሪ አካላትን ግዴታና ኃላፊነቶች ለማስታወስ ነው። በተለይም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመዘዋወር፣ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶችን ጨምሮ ሌሎች በምርጫ ወቅት ትኩረት የሚሹ ሰብአዊ መብቶችን በማረጋገጥ ረገድ የሕግ አስከባሪ አካላት ሚና በዝርዝር ውይይት ተደርጎባቸዋል። የሕግ አስከባሪ ተቋማት ባልደረቦችም ተግባራቸውን ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ ለማከናወን ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል።
ኢሰመኮ በምርጫው ወቅት የሕግ አስከባሪ አካላት በገለልተኝነት ተግባራቸውን በመወጣት የዜጎች መብቶችን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ እንዲሁም ጥሰቶች ሲኖሩ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ በአጽንዖት አሳስቧል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የሕግ አስከባሪ አካላት ሰብአዊ መብቶችን አክብረው ተግባራቸውን ለማከናወን የገቡትን ቃልኪዳን በምርጫው ሂደት በተግባር በመተርጎም የምርጫ ሂደቱ ሰብአዊ መብቶች የተረጋገጡበት እንዲሆን በቁርጠኝነት መስራት ይገባቸዋል” ብለዋል።