የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ከጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ድርጅት (GIZ) ጋር በመተባበር በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የግንዛቤ ማሳደጊያ ዐውደ ጥናት ሚያዝያ 16 እና 17 ቀን 2018 ዓ.ም. አካሂዷል። ዐውደ ጥናቱ ስለ ሽግግር ፍትሕ ጽንሰ ሐሳቦች፣ መርሖች እና አላባውያን፤ ስለ ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት፤ የፖሊሲ ይዘት፤ በሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ኢሰመኮ ስላለው ሚና፤ እንዲሁም በአጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃን በማረጋገጥ ረገድ የዳኝነት አካላት ግንዛቤን ለማሳደግ ያለመ ነው።




በዐውደ ጥናቱ ላይ ነባር እና አዲስ የተሾሙ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ በሽግግር ፍትሕ ሂደት የዳኝነት አካላት ሚና፣ ስልታዊ የሰብአዊ መብቶች ሙግት፣ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ አተገባበር እና ተያያዥ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን የተመለከቱ ገለጻዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።



በውይይቱ ለከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምላሽ በመስጠት ረገድ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች፤ በሽግግር ፍትሕ ስልቶች ቀረጻ እና አተገባበር ሂደት የተጎጂዎችን ፍላጎት፣ እይታ እና ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ጉዳዮች የማካተት አስፈላጊነት፤ እንዲሁም በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ወቅት በመደበኛው የዳኝነት ሥርዓት ውስጥ የሚቋቋሙ ልዩ ችሎትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ተቋማትን ከማቋቋም ጋር ተያይዞ የሚነሱ ስጋቶችን አስቀድሞ በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎች ማስቀመጥን የተመለከቱ ሐሳቦች በስፋት ተነስተዋል።




የውይይቱ ተሳታፊዎች ዐውደ ጥናቱ በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና በዳኝነት ተግባራት መካከል ባለው መስተጋብር ላይ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም መብቶችን መሠረት ያደረገ የዳኝነት ውሳኔ አሰጣጥን (rights-based adjudication) ለማጠናከር እና የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመተግበር የዳኝነት አካላት እና የኢሰመኮ ቀጣይነት ያለው አጋርነት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ ፍርድ ቤቶች ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ መሠረታዊ መብቶችን በማስጠበቅ፣ ገለልተኛ እና ፍትሐዊ ውሳኔ በመስጠት የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውጤታማ አተገባበር ላይ ያላቸውን ቁልፍ ሚና አብራርተዋል። አክለውም፣ በኢትዮጵያ ለተፈጸሙ ከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተገቢ ምላሽ በመስጠት ዘላቂ ሰላም እና የሕግ የበላይነትን ማስፈን እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢሰመኮ አጠቃላይ ለፍትሕ ሥርዓቱ ውጤታማነት እንዲሁም የዳኝነት አካላት በሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚያከናውኗቸውን ተግባራት በመደገፍ ረገድ የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ ይቀጥላል