የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለ6ኛ ጊዜ የሚያካሂደው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር የመጀመሪያው ምዕራፍ በክልል ደረጃ በተካሄደ ውድድር ተጠናቋል፡፡ ውድድሩ በ12 ክልሎች እና በ2 ከተማ አስተዳደሮች ከጥር ወር 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ከ91 ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ 182 ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ ሴቶች ናቸው፡፡





ውድድሩም ምናባዊ በሆነ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ ተማሪዎች የአመልካች እና የተጠሪ ወገንን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር የሚያደርጉበት ሲሆን የመደበኛ ፍርድ ቤት የክርክር ሥርዓትን የሚከተል ሆኖ በተወዳዳሪ ተማሪዎች እና በትምህርት ቤቶች ማኅበረሰብ ዘንድ የሰብአዊ መብቶች ዕውቀትንና ክህሎትን ለመገንባት ያለመ ነው፡፡ የዚህ ዓመት ውድድር “የመማር መብት በግጭት ዐውድ ውስጥ” (The Right to Education in the Context of Armed Conflict) የሚል ርእሰ በተሰጠው የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ያተኩራል።




ተወዳዳሪ ተማሪዎቹ የውድድሩን የመጀመሪያ ክፍል ማለትም በአመልካች እና ተጠሪ በኩል በመሆን ያዘጋጁትን የመከራከሪያ ጽሑፍ በማጠናቀቅ ለክልላዊ የቃል ክርክሩ የደረሱ ሲሆን፤ የቃል ክርክሩም መጋቢት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በተመረጡ ከተሞች እና የከተማ አስተዳደሮች የሕግ እና ሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎችን በዳኝነት በማሳተፍ ተካሂዷል።



በክልል ደረጃ በተካሄደ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር፦
- ከአዲስ አበባ:- እቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት፣
- ከአፋር ክልል:- የነገው ተስፋ እና ወረር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣
- ከአማራ ክልል፦ ሀይሌ ማናስ አካዳሚ፣
- ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፦ ፓሮ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣
- ከማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፦ ሊች ጎጎ ልህቀት አዳሪ ትምህርት ቤት፣
- ከድሬዳዋ ክልል፦ ሳቢያን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣
- ከጋምቤላ ክልል፦ ፒን ይዶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣
- ከሐረሪ ክልል:- ጀግኖች 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣
- ከአሮሚያክልል፦ ሒል ቶፕስ አካዳሚ፣
- ከሲዳማ ክልል፦ ቢኤንቢ የትምህርት ማዕከል፣
- ከሶማሊ ክልል፦ ሸህ አብዱሰላም 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት፣
- ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የማኅበረሰብ ትምህርት ቤት፣
- ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፦ አቡነ ተ/ሃይማኖት ትምህርት ቤት እና
- ከትግራይ ክልል፦ አክሱም አልሙናይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
ውድድሩን በበላይነት ካጠናቀቁት 15 ትምህርት ቤቶች መካከል በጽሑፍ ክርክር የላቀ ነጥብ ያስመዘግቡ 8 ቡድኖች ከሚያዝያ 11 እስከ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አባባ ከተማ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ውድድር ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡




ውድድሩ በክልል ደረጃ በስኬት እንዲጠናቀቅ አሰልጣኝ መምህራን፣ ትምህርት ቤቶች፣ ወላጆች፣ የሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ትምህርት ቢሮዎች እና ባለድርሻ አካላት ጉልህ አስተዋጽዖ አድርገዋል።