ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ከለሊቱ 10፡00 ሰዓት ላይ የታጠቁ ኃይሎች በእንቅልፍ ላይ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ በለኮሱት እሳት እና በተኩስ ከ100 በላይ መገደላቸው በክልሉ ያለው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በከፍተኛ ሁኔታ እተዳከመ መሄዱን እንደሚያሳይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ገለጸ።ኢሰመኮ የጥቃቱን ሂደት በተመለከተ ታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሚመለከታቸው አካላት እና ከተጎጂዎች ጋር በመነጋገር ሲከታተልና ሲያጣራ ቆይቷል። በኩጂ ቀበሌ ከወረዳው መቀመጫ ከሆነችው ቡለን ከተማ 90 ኪ.ሜ. ርቃ የምትገኝ ሲሆን የሺናሻ፣ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ይኖሩባታል። ለቀበሌው የተመደበ የፖሊስ ወይም የፀጥታ ኃይል አለመኖሩን ኮሚሽኑ በክትትሉ መሰረት ተረድቷል። ኮሚሽኑ ሁኔታውን እስካጣራበት ጊዜ ድረስ በቡለን ሆስፒታል 36 ተጎጂዎች እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን አብዛኞዎቹ በጥይት ሌሎቹ በቀስት የቆሰሉ መሆናቸውን ኢሰመኮ በምልከታ አረጋግጧል። በተጨማሪም ሰዎች ጥቃት የደረሰባቸውን ሁኔታ የሚያሳዩና የሚረብሹ የፎቶግራፍ ማስረጃዎች ለኮሚሽኑ ደርሰውታል። በሰው ሕይወት እና በአካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የደረሱ ሰብሎችና የተሰበሰቡ ማሳዎች በእሳት ጋይተዋል። ቢያንስ 18 ያክል ነዶዎች ሲቃጠሉ ማየታቸውን አንድ ተጎጂ አስረድተዋል። በጨላንቆ እና ዶሼ ቀበሌዎች ቤቶች እየተቃጠሉ እንደሆነ ከአካባቢው ለኮሚሽኑ የተላኩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በድባጤ ወረዳ ዶንበን ቀበሌ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ከታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ቀዬአቸውን ጥለው እየተሰደዱ እንደሆነም ኮሚሽኑ ተረድቷል።አካባቢውን በቅርበት እንዲጠብቅ የተመደበው ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት ታኅሣሥ 13 ቀን 2013ዓ.ም. ለማረጋጋት ተግባር ወደቦታው ተልከው የነበሩ አንድ የፌዴራል እና ሁለት የክልሉ አመራሮችን ለማጀብ በሚል አካባቢውን ለቅቆ መሄዱ ታውቋል። ጥቃቱ የጀመረው ይህንኑ ተከትሎ እንደሆነና ሌሊቱን የጀመረው ጥቃት እስከ ቀኑ አጋማሽ ድረስ መዝለቁንም ለማወቅ ተችሏል። ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ተጎጂዎች እንደሚሉት በጥቃቱ ከሞቱ ሰዎች መካከል አብዛኛው የሺናሻ ተወላጆች ናቸው። ከዚህ ቀደም በነበሩ ጥቃቶች ፈጻሚዎቹ ከ”ጫካ” የሚመጡ ሰዎች የነበሩ ቢሆንም፣ በዚህኛው ጥቃት “በስምና በመልክ የሚያውቋቸው” የበኩጂ ቀበሌ ነዋሪዎች ጭምር መሳተፋቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ተጎጂዎች ገልጸዋል።
ኢሰመኮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚከሰቱ ጥቃቶችን ተደጋጋሚነትና የክልሉን ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ አስመልክቶ፣ የፌዴራሉንና የክልሉን መንግሥታት የተጠናከረ ትብብርና ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻ ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወሳል። ይሁንና ጥቃቶቹ በመልክ እና በስፋት እየተባባሱ መጥተዋል። ስለሆነም፣በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸውን እና ለተፈናቀሉ ሰዎች የህክምና እና ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ፣ እንዲሁም ተገቢው ማጣራትና ጥቃቱን ባለመከላከልም ሆነ በሌላ መልኩ ጥቃቱን የፈጸሙና ያባባሱ ሰዎችን ሕግ ፊት የማቅረብ ሂደት ከወዲሁ እንዲጀመር ኮሚሽኑ ያሳስባል። በአካባቢው የሚገኘውን የፀጥታ ኃይልና መዋቅር የሰዎችን ደኅንነት ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በከፍተኛ ደረጃ በአፋጣኝ እንዲጠናከር ኢሰመኮ ጥሪ ያቀርባል።