የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት አንቀጽ 5 (3) እና (4) 

  • እኩልነትን ለማስፋፋትና አድሎዊ ልዩነትን ለማስወገድ ዓላማ ተዋዋይ ሀገራት ተመጣጣኝ ማመቻቸት መደረጉን ለማረጋገጥ ተገቢ የሆነውን ማንኛውንም እርምጃ መውሰድ አለባቸው።
  • የአካል ጉዳተኞችን ተጨባጭ እኩልነት ለማፋጠን ወይም ለማሳካት አስፈላጊ በመሆናቸው የሚወሰዱ የተለዩ እርምጃዎች በዚህ ስምምነት ድንጋጌዎች መሠረት አድሎአዊ ልዩነቶች ተደርገው አይወሰዱም።

የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 6፤ አንቀጽ 23

  • ተመጣጣኝ ማመቻቸት በአካል ጉዳተኝነት ዐውድ ውስጥ ወዲያውኑ ተፈጻሚ ሊሆን የሚገባው አድሏዊ ልዩነት ያለማድረግ ግዴታ አካል ነው። የተመጣጣኝ ማመቻቸት ምሳሌዎች ነባር መገልገያዎችን እና መረጃዎችን ለአካል ጉዳተኛው ተደራሽ የማድረግ፤ መሣሪያዎችን የማስተካከል፤ ተግባራትን እንደገና የማደራጀት፤ የሥራ መርኃ ግብሮችን የማሻሻል፤ የትምህርት ሥርዓትን፣ የመማሪያ ቁሳቁሶችን እንዲሁም የማስተማሪያ ስልቶችን የማስተካከል፤ የሕክምና ሂደቶችን የማስተካከል ወይም ኢ-ተመጣጣኝ ወይም አግባብ ያልሆነ ግዴታን በማያስከትል ሁኔታ አካል ጉዳተኛው ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን እንዲያገኝ የማስቻል እርምጃዎችን ይጨምራሉ።