የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኮላቦሬሽን ኦን ኢንተርናሽናል አይ ሲቲ ፖሊሲ ፎር ኢስት ኤንድ ሳውዘርን አፍሪካ (Collaboration on International ICT Policy for East and Southern Africa) ጋር በመተባበር ቴክኖሎጂ እና ሰብአዊ መብቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ከኮሚሽኑ የከተሞች ጽሕፈት ቤቶች እና ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች ታኀሣሥ 4 እና 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሰጥቷል፡፡
ስልጠናው የቴክኖሎጂ እና ሰብአዊ መብቶች ግንኙነት ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (artificial intelligence) እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ክትትል (surveillance) ከጋዜጠኞች ደኀንነት፣ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን ከማጎልበት እንዲሁም ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃና መስፋፋት ከሚኖራቸው ሚና አንጻር የዳሰሰ ነበር። በተጨማሪም መረጃ የማግኘት መብትን አስመልክቶ ያሉ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ብሔራዊ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎች፣ በመብቱ አተገባባር ዙሪያ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች እንዲሁም የቴክኖሎጂ መስፋፋት መረጃ ከማግኘት መብት አንጻር የሚኖረውን ሚና አካቷል።
ለሁለት ቀናት በቆየው ስልጠና በኢትዮጵያ የኢንተርኔት መስፋፋትና አካታችነትን እንዲሁም የዲጂታል ምህዳሩን ለመቆጣጠር በተቀረጹ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎች ዙሪያ የተከናወኑ ጥናቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። በመጨረሻም ኮሚሽኑ የቴክኖሎጂን መስፋፋት መሠረት አድርገው እየዳበሩ የሚገኙ መብቶች እና በቴክኖሎጂ እገዛ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል እና ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን የሚችልባቸውን መንገዶች አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል።
የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ- ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እድገት ለሰብአዊ መብቶች መከበር ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን በተለይም ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የመሰብሰብ መብትን ከማስፋፋት አንጻር ያለውን ጉልህ ሚና አስገንዝበዋል። ዶ/ር አብዲ የቴክኖሎጂው መስፋፋት ለሰብአዊ መብቶች መከበር የሚያበረክተው አስተዋጽዖ እንዳለ ሆኖ የመብቶች አተገባበር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያመጣ እንደሚችል በተለይም ሐሰተኛ መረጃን እና የጥላቻ ንግግርን በማስፋፋት ረገድ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና መረጃ የማግኘት መብት ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ቴክኖሎጂ የሰብአዊ መብቶችን ግንዛቤ ከማስፋፋት ጎን ለጎን ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች አንጻር ሲታይ ኢሰመኮ ከበይነ መረብ መስፋፋት ጋር የተያያዙ ሰብአዊ መብቶችን የማስተዋወቅ ዐቅሙን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።