የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ ከተማ፣ እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የአስገድዶ መሰወር ሁኔታን ሊያቋቁሙ በሚችሉ እና ያሉበት ሳይገለጽ በተራዘመ እስር ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ሁኔታ በተመለከተ የሚደርሱትን አቤቱታዎችና ከሚመለከታቸው የመንግሥት የጸጥታ ኃላፊዎች የሚሰጡ ምላሾችን መሠረት በማድረግ፣ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. እና ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣቸው መግለጫዎች፣ እንዲሁም ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት የድርጊቱ አሳሳቢነት የቀጠለ መሆኑን እና ይህንን ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወሳል። በተጨማሪም እ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 10 ቀን 2023 የታሰበውን 75ኛው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን በማስመልከት፣ መንግሥት ሀገራዊውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል እርምጃዎች እንደሚወስድ ቁርጠኝነቱን ከገለጸበት (Universal Declaration of Human Rights- Pledges) ጉዳዮች አንዱ ዓለም አቀፉን ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ድርጊት የመጠበቅ ስምምነት ማጽደቅ መሆኑ የሚታወስ ነው።
ይህንን በተመለከተ ኢሰመኮ የተለያዩ ማብራሪያዎችን በተለያዩ መድረኮች ማሰራጨትን ጨምሮ በርካታ ክትትሎችን እና ውትወታዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች መሠረት አባል በሆነችባቸው እና ሪፖርት በምታቀርብባቸው አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተቋማትም ኢሰመኮ ከፍተኛ የውትወታ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል። በተለይም ከመስከረም ወር እስከ ጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም. በተካሄደው 57ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ኢሰመኮ የአስገድዶ መሰወር ድርጊቶች መስፋፋት አሳሳቢነት መቀጠል አስመልክቶ ያቀረበውን የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት ተከትሎ መንግሥት በሰጠው ምላሽ፣ የችግሩን አሳሳቢነት በማስታወስ “ኢትዮጵያ ይህንን ድርጊት በዘላቂነት ለማስቆም ዓለም አቀፍ ግዴታዎቿን መወጣትን ጨምሮ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እንደሚሠራ” (1፡48፡42 ላይ) በድጋሚ ገልጿል።
ኢሰመኮ ያሉበት ሳይገለጽ በተራዘመ እስር ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ እና የአስገድዶ መሰወር ሁኔታን ሊያቋቁሙ በሚችሉ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ሁኔታ በተመለከተ የሚያደርገውን ክትትል የሚቀጥል ሲሆን፣ በተለይም ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተወስደው ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የቆዩ መሆናቸው የተገለጸ ከ52 በላይ የሆኑ ሰዎችን የተመለከቱ አቤቱታዎችን መርምሮ ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ቀን ድረስ 44 ሰዎች ከ1 ወር እስከ 9 ወር በተለያዩ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ከቆዩ በኋላ መለቀቃቸውን ማወቅ ተችሏል። ሆኖም ኢሰመኮ ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ በተራዘመ እስር፣ መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች፣ ብሎም በአስገድዶ መሰወር ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖ የቀጠለ እና በተለይም መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች ውስጥ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ኃላፊዎችን እንዲሁም የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የዐይን ምስክሮችን እና የተለቀቁ ሰዎችን በማነጋገር መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን አሰባስቧል።
ተጎጂዎች በአብዛኛው ሰሌዳ በሌላቸው ተሽከርካሪዎችና በታጠቁ ሲቪል ወይም የደንብ ልብስ በለበሱ የጸጥታ አካላት ተገቢውን የሕግ ሥነ ሥርዓት ባልተከተለ ሁኔታ በግዳጅ የተያዙ መሆናቸውን እና በእስር የቆዩበትን ቦታ የማያውቁ፣ በቂ ምግብና ውሃ የማይቀርብላቸው የነበሩ፣ እንዲሁም ለየብቻቸው ተለይተው ተይዘው የቆዩ መሆናቸውን ያስረዳሉ። ከተጎጂዎቹ መካከል የመለቀቃቸውን ሂደት ሲያስረዱ በምሽት ዐይናቸው ተሸፍኖ በተሽከርካሪ ከተጫኑ በኋላ በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች እንዲወርዱ ተደርገው እና “ለመጓጓዣ” በሚል ከ300 እስከ 1000 ብር ተሰጥቷቸው የተለቀቁ መኖራቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ሁሉም ተጎጂዎች በእራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት፣ እንዲሁም ከፍተኛ የሥነ ልቦና ቀውስ መድረሱን እና በሥጋት መኖራቸውን ያስረዳሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ካለፉ እና ኢሰመኮ በክትትልና ምርመራው ካነጋገራቸው ሰዎች መካከል ለምሳሌ የሚከተሉት፣ እንዳግባብነቱ እና በተጎጂዎች ፈቃድ ለማሳያነት ተመላክተዋል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ለተጎጂዎቹ እና ለቤተሰቦቻቸው ደኅንነት ሲባል የተጎጂዎችን ማንነት የሚገልጹ መረጃዎች አልተመላከቱም።
የአስገድዶ መሰወር ሁኔታን ሊያቋቁም በሚችል ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ተጎጂዎች
ኢሰመኮ እነዚህን እና ሌሎች በተመሳሳይ ሁኔታ ያሉ ተጎጂዎችን የተመለከቱ አቤቱታዎች መሠረት በማድረግ ከግንቦት ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ባደረገው ምርመራ እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በተሰጠው ምላሽ እነዚህ ሰዎች በመደበኛ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ስፍራ ውስጥ አለመሆናቸውን ማወቅ ተችሏል። ኢሰመኮ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከተቀበላቸው አቤቱታዎች መካከል አሁንም ያሉበት ቦታ ያልታወቀ 6 ሰዎች ሁኔታን በተመለከተ ከሚመለከታቸው የመንግሥት የጸጥታ እና የአስተዳደር አካላት ምላሽ ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት የሚቀጥል ነው።
- አቶ መንበረ ቸኮል ምስጋናው፣ የግንባታ ባለሙያ፣ የ7 እና የ4 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 2 ሕፃናት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ “ሰፈራ” ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በጸጥታ አካላት ሰሌዳ በሌለው ተሽከርካሪ የተወሰዱ ሲሆን፣ ያሉበት ቦታ እና ሁኔታ የማይታወቅ በመሆኑ ቤተሰቦቻቸው ለከፍተኛ ጭንቀትና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ተጋልጠው ይገኛሉ።
- አቶ ዘላለም ግሩም ፍላቴ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባልና አሽከርካሪ ሲሆኑ፣ ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ፣ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ፣ ልዩ ስሙ “ዲቦራ ትምህርት ቤት” ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በጸጥታ አካላት ሰሌዳ ቁጥሩ ባልታወቀ ተሽከርካሪ ከተወሰዱ ጀምሮ፣ ያሉበት ቦታ እና ሁኔታ የማይታወቅ በመሆኑ ቤተሰቦቻቸው በከፍተኛ ጭንቀትና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ውስጥ ይገኛሉ።
በተለያየ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ወይም ያሉበት ሳይታወቅ በተራዘመ እስር ሁኔታ ቆይተው የተለቀቁ፦
- አቶ አማረ ግዳፍ፣ ባለ3 እግር ተሽከርካሪ በተለምዶ “ባጃጅ” በማሽከርከር ሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆኑ መጋቢት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ በአዲስ አበባ ከተማ፣ የካ ክፍለ ከተማ፣ በተለምዶ “ወሰን መስቀለኛ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 6 የሲቪል ልብስ እና 1 የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ በለበሱ ሰዎች እና ሰሌዳ በሌለው ተሽከርካሪ ተወስደው፣ ላለፉት 6 ወራት ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ ቆይተው በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም. ተለቀዋል።
- አቶ ዓለማየሁ ከፈለ ተሰማ የተባሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ነሐሴ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 1 በተለምዶ “ፍላሚንጎ” በሚባለው አካባቢ ሲቪል ልብስ ለብሰው መታወቂያ በያዙ 6 የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተወስደው፣ በሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም. ተለቀዋል።
- አቶ መቼምጌታ አንዱዓለም፣ ባለትዳርና የ2 ሕፃናት ልጆች አባት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ነሐሴ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡00 ሰዓት አካባቢ “ብስራተ ገብርኤል” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የታክሲ አገልግሎት ከሚሰጡበት አካባቢ ከነተሽከርካሪያቸው የሲቪል ልብስ በለበሱ የጸጥታ አካላት ተወስደው፣ በተለምዶ “ራሺያ ካምፕ” ተብሎ በሚጠራው የመከላከያ ሰራዊት አባላት መኖሪያ ለ7 ወራት ከቆዩ በኋላ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ተለቀዋል።
- ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የቤተሰብ አስተዳዳሪ እና የልጆች አባት የሆኑ ተጎጂ፣ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ገደማ ከግል የሥራ ቦታቸው ሲቪል እና የደንብ ልብስ ለብሰው ቀይ ቦኔት ባደረጉ የጸጥታ አባላት ተይዘው፣ ሰሌዳ በሌለው ተሽከርካሪ ጦር ኃይሎች አካባቢ በተለምዶ “ራሺያ ካምፕ” ተብሎ በሚጠራው የመከላከያ ሰራዊት አባላት መኖሪያ እንደቆዩ አስረድተዋል። ከዚያ ቀን ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ እና የፌዴራል ፖሊስ ጣቢያዎች ቢያፈላልጓቸውም በምን ምክንያት እንደተያዙ ለማወቅ ሳይቻል፣ ለ2 ወራት ከቆዩ በኋላ ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለቀዋል።
- ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላው ተጎጂ ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሚሠሩበት አካባቢ ሲቪል እና የደንብ ልብስ ለብሰው ቀይ ቦኔት ባደረጉ የጸጥታ አካላት በተለምዶ “ፓትሮል” በሚባል ተሽከርካሪ በግዳጅ ተወስደው ባልታወቀ ቦታ ከቆዩ በኋላ፣ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለቀዋል።
- ሌላ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ተጎጂ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ እና ባለትዳር ሲሆኑ፣ ታኅሣሥ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. እኩለ ቀን ላይ በተለምዶ “ስታዲየም” በሚባለው አካባቢ ከሚሠሩበት ቦታ ሲቪል በለበሱና ሽጉጥ በታጠቁ፣ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ በለበሱና ቀይ ቦኔት ባደረጉ የጸጥታ አካላት ሰሌዳ ቁጥር በሌላቸው ዳለቻ ቀለም እንደሆኑ በተገለጸና በተለምዶ “ሎንግቤዝ” እና “ፓትሮል” ተብለው በሚጠሩ መኪናዎች ተጭነው ተወስደው፣ ከ6 ወራት እስር በኋላ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለቀዋል።
- በተመሳሳይ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ተጎጂ ከግል የሥራ ቦታቸው የተወሰኑት ሲቪል እና ሌሎች የደንብ ልብስ በለበሱና በታጠቁ የጸጥታ አካላት መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ከተያዙ በኋላ፣ ዐይናቸውን በጨርቅ ተሸፍነው ተወስደው ያሉበት ሳይታወቅ እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቆዩ በኋላ፣ በድጋሚ ዐይናቸውን በጨርቅ ተሸፍነው አዲስ አበባ ከተማ፣ “ኃይሌ ጋርመንት” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንዲወርዱ መደረጋቸውን አስረድተዋል።
መደበኛ ባልሆነ ማቆያ ቦታዎች ውስጥ፣ ያሉበት ሳይገለጽ እንዲቆዩ በተደረጉ እና በአስገድዶ መሰወር ሁኔታዎች ውስጥ በሚቆዩ ሰዎች ላይ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች
ሁሉም ተጎጂዎች በእነዚህ መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች የነበረውን ሁኔታ በተመለከተ መሠረታዊ የመጸዳጃ፣ የመኝታ እና የንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦቶች አለመኖራቸውን፣ የቤተሰብ ሁኔታን ማወቅ ሳይችሉ እና ለቤተሰብ ያሉበት ቦታ ሳይገለጽ፣ እንዲሁም ምግብ እና የመጠጥ አቅርቦቱ እጅግ የተጓደለበት ቦታ የቆዩ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ከላይ የተጠቀሱት ተጎጂ አቶ መቼምጌታ ተይዘው የቆዩበትን ሁኔታ በተመለከተ “በቂ ምግብ የማይቀርብበት፣ ከፍተኛ የሆነ የውሃ ችግር ያለበት፣ ሰዎች ሕመም ሲገጥማቸው ሕክምና ማግኘት የማይችሉበት፣ ምንም ዐይነት የቤተሰብ ጥየቃ የማይፈቀድበት እንዲሁም ከፍራሽ ውጪ የመኝታ አልባሳት የሌሉበት” መሆኑን ለኢሰመኮ ገልጸዋል። “ለ7 ወራት አካባቢ ተይዤ ስቆይ በቦታው በአጠቃላይ ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎች ተይዘው እንደነበር ተመልክቻለሁ፤ ለ1 ወር ከ20 ቀናት ለብቻዬ ተለይቼ ታስሬ የነበረ ሲሆን፣ “መረጃ አውጣ” በሚል ድብደባ ተፈጽሞብኛል” ብለዋል። በተጨማሪም “መረጃ አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች በቅጥር ግቢው ውስጥ በሚገኝ ሕንጻ ምድር ቤት ውስጥ ይታሰሩ እንደነበር” መመልከታቸውን ይናገራሉ።
አቶ ሞላ ባዘዘው የተባሉ ሌላ ተጎጂ የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡30 ሰዓት አካባቢ ከሥራ ወደ ቤት ሲመለሱ “ሣር ቤት አደባባይ” በሚባለው ስፍራ ጭንብል የለበሱ 4 ደኅንነቶችና 1 ሾፌር የመኪና መንገድ በመዝጋት ከግል መኪናቸው አስወርደው በተለምዶ “ፒክ አፕ” በሚባል መኪና እንደወሰዷቸው ለኢሰመኮ አስረድተዋል። በዕለቱ ቄራ አካባቢ በሚገኝው የኦሮሚያ ቢሮ ግቢ በማስገባት እስከ 11፡00 ሰዓት በመኪና ውስጥ ያቆዩዋቸው መሆኑን ያስረዳሉ። በማስቀጠልም ከቀኑ 11፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ድረስ በቡልጋሪያ መስቀለኛ መንገድ ወደ ሜክሲኮ በሚወስደው ጎዳና ላይ መኪና ውስጥ አቆይተው፣ ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ሲሆን እስከ 15 ደቂቃ በፈጀ ጉዞ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ወደ ማያውቁት ቦታ መወሰዳቸውን ገልጸዋል። የተያዙበት ክፍል 2 በ2 ካሬ ሜትር የሆነ፣ መስኮትና መብራት የሌለው ጨለማ እንደነበር፤ ወለሉ እርጥበት አዘል በመሆኑና ፍራሹ በመርጠቡ ለመተኛት አዳጋች እንደነበር፤ በቀን አንድ ጊዜ ሌሊት 7፡00 ሰዓት ላይ ለመጸዳዳት ጸጥታ አባላቱም ሆነ እራሳቸው ጭምብል ለብሰው እንደሚወስዷቸው አብራርተው፣ ለ16 ቀናት በዚህ ስፍራ ለብቻቸው ተይዘው የቆዩ መሆኑን ይገልጻሉ። በእነዚህ 16 ቀናት እስር ጊዜ ውስጥ ድብደባ ባይፈጸምባቸውም፣ በየ 2 ቀናት ልዩነት፣ 2 የጸጥታ አባላት ፊት የሚሸፍን ጭንብል ለብሰው እንደሚመጡ እና “ከፋኖ ጋር ይሠራል ብለን ለመከላከያ አሳልፈን እንሰጥሃለን” በማለት ያስፈራሯቸው የነበረ መሆኑን ገልጸዋል። የመለቀቃቸውን ሁኔታ በተመለከተም ከዚህ ቦታው እስካሁን ካልታወቀ ማቆያ ስፍራ የ15 ደቂቃ ያክል እንደፈጀ በሚገምቱት የመኪና ጉዞ በኋላ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተወስደው መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የተለቀቁ መሆኑን ያስረዳሉ።
አንድ ሌላ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ እና ከሚያዝያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በአዋሽ አርባ አካባቢ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የምዕራብ እዝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ የቆዩ አቤቱታ አቅራቢ ሲያስረዱ፣ ወደቦታው የተወሰዱት ለቤተሰቦቻቸው ሳይነገር መሆኑን እና በቆይታቸውም በቂ ምግብ እና ምቹ መኝታ ካለመኖሩ በተጨማሪ የአካባቢው አየር ከፍተኛ ሙቀት ያለበት እና መርዛማና ተናዳፊ እንስሳት የነበሩበት ቦታ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ሁኔታ ለ2 ወራት ከቆዩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ እንዲመለሱ ተደርገው ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. መለቀቃቸውን አስረድተዋል።
ሌላኛው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ተጎጂ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. 2 የሀገር መከላከያ ዩኒፎርም የለበሱና 2 ሲቪል የለበሱ ግለሰቦች ዐይናቸውን በጨርቅ በመሸፈን የወሰዷቸው መሆኑን እና ባላወቁት ቦታ በእስር የቆዩ መሆኑን ለኢሰመኮ አስረድተዋል። ተሰውረው በነበሩበት ጊዜ ድብደባ የተፈጸመባቸው መሆኑን እና በደረሰባቸው ድብደባ ምክንያትና ዐይናቸው ለበርካታ ቀናት በጨርቅ ተሸፍኖ በመቆየቱ ለከፍተኛ ሕመም መዳረጋቸውን፣ በሰውነታቸው ላይ ጠባሳ መኖሩንና የወሰዷቸው የጸጥታ አካላት ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በመንገድ ላይ ትተዋቸው የሄዱ መሆኑን ለኢሰመኮ ገልጸዋል።
ከተጎጂዎች የተወሰኑት ለየብቻቸው ተለይተው ታስረው የቆዩ መሆኑን፣ ሌሎች ደግሞ “ለምርመራ” በሚል ከማቆያ ክፍላቸው በማስወጣት ድብደባና ማስፈራራት ይፈጸምባቸው እንደነበር አስረድተዋል።
አፋጣኝ ትኩረት የሚሹ ተጨማሪ አሳሳቢ ሁኔታዎች
ከቀናት እስከ ወራት ለቆየ፣ ትክክለኛ አድራሻውን ማወቅ ባልተቻለ እና መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች በእስር ቆይተው ከተለቀቁ ሰዎች መካከል፣ የያዟቸው ሰዎች ገንዘብ ከፍለው ሊለቀቁ የሚችሉ መሆናቸውን የገለጹ እና አንዳንዶቹም በቤተሰብ አማካኝነት በብዙ ሺህዎች የሚቆጠር ብር የከፈሉ መሆኑን ያስረዱ መኖራቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት እና አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ መሆኑን በተጨማሪ የሚያጠናክር ነው። ለምሳሌ አንድ ተጎጂ “እንለቅሃለን ስላሉኝ መርማሪ የነበረው የሻለቃ ማዕረግ ያለው ሰው በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ገንዘብ ከቤተሰቤ ተቀብሏል” ያሉ ሲሆን፣ ከዛም ሳይለቋቸው እንደቀሩና የጀነራል ማዕረግ እንዳላቸው የተገለጸ ሌላው ሰው ደግሞ “በቦታው በእስር ከነበሩ መካከል በተመሳሳይ መንገድ ገንዘብ የከፈሉ ሰዎችን ቃል ከተቀበሉ በኋላ ከ“ፋኖ” ጋር ትብብር እንዳያደርጉ ማስጠንቀቂያ ከሰጧቸው ከጥቂት ቀናት በኋላ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. መለቀቃቸውን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ከተጎጂዎች እና ከአቤቱታ አቅራቢዎች መካከል ከመደበኛ የማቆያ ቦታ፣ በአንዳንድ ሁኔታዎችም የፍርድ ቤት ሂደት ተቋርጦ መደበኛ ወዳልሆኑ ማቆያ ቦታዎች የተወሰዱ መኖራቸው ሌላኛው እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በአዋሽ አርባ ለ2 ወራት እንዲቆዩ የተደረጉት ተጎጂ ሲያስረዱ፦ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሚሠሩበት የግል ድርጅት አካባቢ በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር ውለው አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መቆየታቸውን፣ እንዲሁም መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ቀጠሮ ለመጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ተሰጥቶ የነበረ መሆኑን፣ ሆኖም በዕለቱ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና መዝገቡ የተቋረጠ መሆኑን ተነግሯቸው ወደ አዋሽ አርባ የተዛወሩት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስከ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ከቆዩ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግሥት አካላት ምላሽ
ኢሰመኮ በመንግሥት የጸጥታ አካላት ተወስደው ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የቆዩ ሰዎችን ሁኔታ በተመለከተ ከላይ ከተጠቀሱት የሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት በመነጋገር፣ በፌዴራልና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተደጋጋሚ ጉብኝት በማድረግ፣ እንዲሁም በመደበኛ ማቆያዎች ውስጥ አለመኖራቸውን በማረጋገጥ ክትትል ያደርጋል። እንዲሁም በጽሑፍ ምላሽ እንዲሰጡ እና ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች ላይ ምክረ ሐሳቦችን በመስጠት እና ከበላይ አመራሮች ጋር በመወያየት ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ላይ ይገኛል።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት አስተዳደር ሥር ባሉ መደበኛ ያልሆኑ ማቆያ ቦታዎች ተይዘው ያሉ መሆናቸው የተመላከቱ አቤቱታዎችን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምላሽ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ይህ መግለጫ እስከወጣበት ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሳካ ቢሆንም፣ ጥረቱ የሚቀጥል ይሆናል።
ምክረ ሐሳቦች
- አሁንም ያሉበት ቦታ በማይታወቅ፣ ብሎም የአስገድዶ መሰወርን ሊያቋቁም በሚችል ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን በተመለከተ የሚመለከታቸው የመንግሥት የጸጥታ አካላት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጡ ይገባል።
- ሰዎችን መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች ማቆየት ከሕግ እና መደበኛ አስተዳደር ውጪ በመሆኑ፣ እንዲሁም በእነዚህ ቦታዎች ውስጥ እንዲቆዩ የሚደረጉ ሰዎችን አያያዝ እና የእስር ሁኔታ በተመለከተ አካላዊ ጉብኝት እና ምርመራ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ተደራሽ አለመሆናቸው፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ለተጎጂዎች ፍትሕ ለማሰጠት አዳጋች የሚያደርጋቸው በመሆኑ፣ እንዲሁም በአካል የጎበኛቸውን መደበኛ ያልሆኑ ቦታዎች መሠረት በማድረግ እነዚህ ቦታዎች መሠረተ ልማት እና መሠረታዊ አቅርቦት ያልተሟሉባቸው እና ሰዎችን ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚዳርጉ መሆናቸውን ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሪፖርት ማድረጉ የሚታወስ ነው። ስለሆነም አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች ሰዎችን የማቆየትና የማሰር ተግባር እንዲቆም ሁሉም የሚመለከታቸው የሕግ እና የጸጥታ አካላት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ኢሰመኮ በድጋሚ ያሳስባል።
- ሰዎችን የመያዝ እና በእስር የማቆየት ሥልጣን በሕግ ያልተሰጣቸው ተቋማት ወይም መደበኛ ያልሆኑ መዋቅሮች (ad hoc structures) እና ይህንን ተግባር በሚፈጽሙ አባላት ላይ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እና በአፋጣኝ ሊቆም የሚገባ ነው።
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ያሉበት ሳይገለጽ ወይም በማይታወቅ ቦታ፣ በአብዛኛው ጊዜ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች እንዲቆዩ የሚደረጉ፣ ብሎም የአስገድዶ መሰወር ሁኔታን ሊያቋቁሙ የሚችሉ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች በቀጥታ ከሚደርስባቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በተጨማሪ፣ በቤተሰቦች ላይ የሚደርሰው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት፣ እንዲሁም እውነቱን የማወቅ መብት ጥሰት እና ተያያዥ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የድርጊቱን አስከፊነት እንደሚያባብሰው አስታውሰው፣ አሁንም ያሉበት ሁኔታ የማይታወቁ ሰዎችን ጉዳይ በተመለከተ የጸጥታ አካላቱ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም አሠራራቸው፣ አስተዳደራቸው፣ አድራሻቸው ግልጽ ባልሆነ፣ መሠረተ ልማት ባልተሟላበት እና በሌሎች ሁኔታዎች ሳቢያ መደበኛ ያልሆኑ ማቆያ ቦታዎች ሰዎችን ለከፍተኛ ሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚዳርጉበት ዕድል ሰፊ እንዲሁም ተገቢውን ምርመራ እና ተጠያቂነት ለማስገኘት አዳጋች በመሆናቸው ይህ አሠራር ሊቆም እንደሚገባ ገልጸዋል። “ዓለም አቀፉ ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የወጣው ስምምነት፣ ድርጊቱን ለመከላከል ጭምር በመንግሥት ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎችንም የሚያካትት በመሆኑ እና እ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 10 ቀን 2023 75ኛውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን በማስመልከት በአዲስ መልኩ በተገባው ቃል መሠረት ይህንን ስምምነት ኢትዮጵያ እንድታጸድቅ ኢሰመኮ የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል” ብለዋል።