የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች የሴቶች፣ የሕጻናት እና የአካል ጉዳተኞችን ፍትሕ የማግኘት መብት በማስከበር ረገድ የፍርድ ቤቶችን ሚና አስመልክቶ ስልጠና ሰጥቷል።

ስልጠናው የተሰጠው በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የክልሉ ዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ 3ኛ ቀን ውሎ ላይ ነው።

በስልጠናው የኢሰመኮ ባለሙያዎች የሴቶች፣ ሕፃናት እና አካል ጉዳተኞችን ፍትሕ የማግኘት መብት በማስከበር ረገድ የፍርድ ቤቶችን ሚና አብራርተዋል።

የኮሚሽኑ የሴቶች መብት ባለሙያ ወ/ሮ ጎጃም አበበ ፍርድ ቤቶች ያለ አድሎ ምቹ የችሎት ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ባለሞያዋ ሴቶት እና ህፃናት እድሜያቸውን፣ ጾታቸው እና የአካል ጉዳታቸውን መሠረት ያደረገ አድሎ ሳይደረግባቸው ፍትሐዊ የሆነ አገልግሎት ማግኘትን፣ የሕግ አገልግሎት ድጋፍ እና ግንዛቤ ማግኘትን እና በምቹ ችሎቶች መስተናገድን የሚያካትት መሆኑን ገልጸው፣ ፍርድ ቤቶች እነዚህ አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ የሚገባቸው ስለመሆኑ አንስተዋል።

ዳኞች ውሳኔ በሚሰጡበት ወቅት ለሕፃናት በጎ እድል (best interest of the child) ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

እንዲሁም ፍርድ ቤቶች እንደ CEDAW እና CRC ያሉ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶችን መሠረት አድርገው መስራት እንደሚገባቸው አብራርተዋል።

በሌላ በኩል የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች መብት ባለሙያ አቶ አረጋ ሽፈራው አካል ጉዳተኞች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ዘርዝረዋል።

ችግሮቹን ለመቅረፍ ፍርድ ቤቶች የአካባቢ ምቹነትን ማረጋገጥ እና የቋንቋ ተግዳሮቶችን መፍታት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን በመመደብ ተቋማዊ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አስንተዋል።

ይህ ስልጠና የዳኞችን ሙያዊ አቅም በማሳደግ ፍትሐዊ እና ሰብዓዊ መብትን ያከበረ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል።

ፎቶ ምንጭ ፦የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት