የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ማለትም በከፍተኛ ጥበቃ (አባ ሳሙኤል)፣ በቂሊንጦ ጊዜ ቀጠሮ ማረፊያ፣ በቃሊቲ የሴቶች ማረሚያ እንዲሁም በዝዋይ ተሐድሶ ማረሚያ ማዕከል ያካሄደውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክትትል ግኝቶችና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን አፈጻጸም በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ማካሄድ ጀምሯል።
በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለው በዚህ የሁለት ቀን የምክክሩ መድረክ ላይ የኢሰመኮ ኮሚሽነሮችና አመራሮች እንዲሁም የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የፍትሕ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ምክክሩን በንግግር የከፈቱት በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ስልጠና ኮሚሽነር በዳሳ ለሜሳ፣ በማረሚያ ቤቶች የሚካሄዱ ክትትሎች ተጠናክረው የሰብአዊ መብት አያያዙ እንዲሻሻል መሰል ምክክሮች አስፈላጊ መሆናቸውን ገልፀዋል።






ለክትትል ግኝት ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊነት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ተክሉ ለታ በበኩላቸው በማረሚያ ቤቶች ለሰብአዊ መብቶች አያያዝ መሻሻል ምክክሩ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ምክረሃሳቦቹን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።







የመድረኩ ዋና ዓላማ በማረሚያ ቤቶች የተካሄደውን የክትትል ግኝት መነሻ በማድረግ የታራሚዎችና የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ አያያዝ ሁኔታ በዝርዝር መገምገም፣ እንደ ክፍተት የተለዩ ጉዳዮች የሚፈቱበትን አቅጣጫ ማመላከትና በተሰጡት ምክረ ሐሳቦች መሠረት ባለድርሻ አካላት የሚወስዷቸውን እርምጃዎች የያዘ የአንድ ዓመት የድርጊት መርሃ ግብር ማዘጋጀት ነው።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በተዘጋጀው የአንድ ዓመት የድርጊት መርሃ ግብር ላይ ከሚያደርጉት ውይይት በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ ዞን ማረሚያ ቤትን በመጎብኘት የልምድ ልውውጥ ያደርጋሉ።